የፓናል ውይይት በሀዋሳ

ሰላም ሚኒስቴር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመተባበር "ሃገራዊ እሴቶቻችን ለጠንካራ ሀገር ግንባታ" በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት መድረክ በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል አዘጋጅቷል::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ የፓናል ውይይቱን ተሳታፊዎች እንኳን ደህና መጣችሁ ባሉበት ወቅት እንደተናገሩት በሀገራችን በርካታ መልካም እሴቶች ቢኖሩም በተግባር የሚታየው ግን ሰላምና ሃገራዊ እድገትን የሚፈታተኑ ዘርፈ ብዙ ግጭቶች መሆናቸው ብዙ የቤት ሥራ እንዳለብን ያመላክታል:: ዶ/ር ሳሙኤል አክለው ሀገራችን ላይ ችግር የሆነው የመልካም እሴቶች እጥረት ሳይሆን የሚሉትን የማይኖሩ ሰዎች በመበራከታቸው እንዲሁም ከራሳቸው እሴት ሌላ ብዝሃነትን ለማስተናገድ የሚቸገሩ ሰዎች መኖራቸው በመሆኑ የተሻለ አንድነት ለማምጣት መሰል የውይይትና ሃገራዊ መግባባት መድረኮች እንዲኖሩ ያስገድዳል ብለዋል::

የሰላም ሚኒስቴር ደኤታው አቶ ታዬ ደንዳአ በበኩላቸው "ሃገራዊ እሴቶቻችን ለጠንካራ ሀገር ግንባታ" በሚል ርዕስ የሰላም ተምሳሌት የሆነውና በርካታ ምሁራንን እያፈራ ያለው አንጋፋው ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲና በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ዘመን ተሻጋሪ አሻራውን እያኖረ ያለው ኢዜአ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር የየድርሻቸውን ብሔራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ላደረጉት አስተዋፅኦ ከልብ አመስግነዋል:: በተጨማሪም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙትን ዘመን ተሻጋሪ መልካም እሴቶቻችንን በምሁራን በማስጠናት: በመሰነድ እንዲሁም አዲሱ ትውልድ እንዲያውቀውና እንዲመራበት ለማስቻል የዚህ አይነት የውይይት መድረኮች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ሚኒስትር ደኤታው አስምረውበታል::

ለፓናል ውይይቱ የመነሻ ጥናታዊ ፅሁፎች በዶ/ር ዳኘ ሽብሩ: ዶ/ር ንጉስ በላይ እና ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ የቀረቡ ሲሆን ከሲዳማ ብ/ክ/መንግስትና ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች: መምህራን: የአስተዳደር ሰራተኞችና ተማሪዎች የተውጣጡ ከ120 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል:: በውይይቱም በተለያዩ ምክንያቶች እየተሸረሸሩ ያሉትን መልካም ሃገራዊ እሴቶች እንዴት ማጎልበትና ለጠንካራ ሀገር ግንባታ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ማመቻቸት እንደሚገባ በሰፊው ተነስቷል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et