ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ጋር በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ::
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ በፊርማው ስነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲልም በርካታ ስራዎችን ከቢሮው ጋር ሲሰራ ስለቆየ አሁን የትብብር መግባቢያ መፈራረማችን ለተሻለ አብሮነት ስለሚረዳን ነው ብለዋል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲውና ቢሮው ሁለቱም የትምህርት ዘርፉ የስራ ባለቤት እንደመሆናቸው በትብብር መስራቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል:: ይሄ የራሳችን ተቋም እንጂ ሌላ አይደለምና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትኩረት ዘርፍም እንደመሆኑ ባለን የትምህርት ልህቀት ማዕከል አብረን በትብብር መስራታችን ቀደም ሲል የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከርም አዳዲስ ስራዎችን አብሮ ለመስራትም ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል::
የክልሉ ት/ት ቢሮ የመምህራን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ተክሉ አዱላ በበኩላቸው የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ኮሌጅ በክረምት 1,678 መምህራንን ተቀብሎ በድኅረ ምረቃ የመምህርነት ስልጠና (PGDT) መርሃግብር ላይ እንዲሳተፉ ማድረጉን ጠቁመው በበጋው መርሃግብርም ኮሌጁ በርካታ መምህራንን እያሰለጠነልን ይገኛል ካሉ በኃላ እነዚህንና መሰል የአቅም ማጎልበቻ ሥራዎች በጋራ ለመስራት ትብብራችንን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል:: አቶ ተክሉ ከዚህ የትብብር ውል በኃላ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እያስተማሩ ያሉ ከ6 መቶ በላይ የመምህርነት ስልጠና ያልወሰዱ የአፕላይድ ዲፕሎማ መምህራን ስላሉ እነዚህን መምህራን በአጭርና ረጅም ግዜ ስልጠና ለማብቃት: በትምህርት ዘርፉ ላይ የምርምር ስራዎችን በጋራ ለመስራትና ሌሎች መጠነሰፊ የመምህራን አቅም ማጠናከሪያ ሥራዎችን አብሮ ለመስራት መታቀዱን አስረድተዋል::
በዕለቱ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ኮሌጅን ወክለው የተገኙት ዶ/ር አሸብር ስምምነት መፈራረማችን ከምርምርና መማር ማስተማር እንዲሁም ስልጠናዎች አንፃር ቀድሞም የነበረንን ትብብር የበለጠ ለማጠናከርና ሁለታችንም የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ስራዎችን በቅርበት እንድንከውን ነው ብለዋል::