የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ተካሄደ

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አመታዊውን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር አካሄደ።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በየአመቱ እንደሚያደርገው ሁሉ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በሀዋሳ አየር ማረፊያ አካባቢ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አካላት የተሳተፉበት የችግኝ ተከላ አካሂዷል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አለማችን ከአየር ንብረት መዛባት የተነሳ በክረምት ወራት የጎርፍ መጥለቅለቅ እንዲሁም በበጋ ወራት የሙቀት መጨመርና ድርቅ ሰለባ በመሆኗ ይህንን አደጋ ለመከላከል በአለምአቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ጥበቃ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም በዘንድሮው አመት "ዛሬን ለነገ እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አንድ አካል የሆነው የዛሬው የችግኝ ተከላ ከዛሬ ሁለት አመት በፊት በተካሄደበት ተመሳሳይ ስፍራ ላይ መከናወኑ ቀደም ሲል የተተከሉ ችግኞች ያሉበትን የጽድቀት ደረጃ ለመገምገም እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የችግኝ ተከላው ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሙሉጌታ ዳዲ በበኩላቸው በኢፌዴሪ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት ከአራት አመታት በፊት የተጀመረው "የአረንጓዴ አሻራ" ሀገር አቀፍ መርሃ-ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ስፍራዎች የችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። ዶ/ር ሙሉጌታ ጨምረውም እንደ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተከላ እየተካሄደ የሚገኝበት የአየር ማረፊያ አካባቢ መሬቱ እጅግ የተጎዳ ስለነበረ ወደ ሀዋሳ ሐይቅ የሚገባውን ደለል ለመከላከል እንዲሁም የአርሶ አደሮች መሬትን ከመንሸራተት አደጋ ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን እና ቀደም ሲል በተሰሩ ስራዎችም ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

በፌዴራል ፖሊስ የዩኒቨርሲቲ ደህንነት መምሪያ ሁለተኛ ሬጂመንት የዩኒቨርሲቲ ሰራዊት አስተዳደር የሆኑት ም/ኮማንደር መንግስቱ ደሳለኝ በመርሃግብሩ ላይ እንዳሉት ሰራዊቱ ዋነኛ ተልዕኮው ከሆነው ወንጀልን መከላከል ጎን ለጎን ሀገርን በሚጠቅሙ መሰል መርሃ-ግብሮች ላይ በንቃት በመሳተፍ የሚታወቅ መሆኑን ገልጸው እንደ ዩኒቨርሲቲ ሰራዊት ደግሞ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ እየተሳተፈ ይቀጥላል ብለዋል።

በመጨረሻም በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የቢሻን ጉራቻ ክ/ከተማ አልጌሪማ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ተሾመ ወዩ ጽ/ቤቱ ከዩኒቨርሲቲው እና ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ በመሆን የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን እና በዚህም የተነሳ ወደ ሀዋሳ ሐይቅ ይገባ የነበረውን ደለል መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል። ችግኝን መትከል ብቻ በቂ ባለመሆኑ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ እንዲጸድቁ መርዳት የሁላችንም ድርሻ በመሆኑ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች በተለያየ ጊዜ ወደ አካባቢው ተመልሶ በመምጣት ክትትል እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et