የርቀት ትምህርት መማሪያ መፃህፍት ረቂቅ ግምገማ ተካሄደ

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ  በርቀት መርሃ ግብር የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት ረቂቅ ላይ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ አዘጋጀ፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ልህቀት ማዕከል ከአዲስ አበባ፣ ባህርዳር እና ጂማ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በትምህርት ሚኒስቴር ባለቤትነት ሲያዘጋጅ የቆየውን የርቀት መርሃ ግብር ከ9ኛ-12ኛ ክፍል የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት የመጨረሻ ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት አገር አቀፍ ግምገማዊ የምክክር መድረክ ከሐምሌ 8-11/2015 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ አዘጋጅቷል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንደገለፁት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን በማስተባበር ከዚህ ቀደም ከ9ኛ-12ኛ ክፍል እንዲሁም በተመረጡ የትምህርት አይነቶች ከ1ኛ-8ኛ ክፍሎች የተማሪ መማሪያና የመምህሩ መምሪያ መጽሐፍትን በማዘጋጀት ወደ ሙከራ ትግበራ እንዲገቡ ያደረገ ሲሆን የጎልማሶች ክህሎት ማሳደጊያ ሞጁሎችንም አዘጋጅቶ ለትምህርት ሚኒስቴር በመላክ በተሰጡት አስተያየቶች መሰረት ማስተካከያ ተደርጎባቸው ዝግጅታቸው እየተገባደደ መሆኑን አውስተዋል:: በዚህ መድረክም ከዚህ በፊት የተዘጋጁትን በርቀት መርሃ ግብር ከ9ኛ-12ኛ ክፍል የተማሪ መማሪያ መፃሕፍት ረቂቅ ለግምገማ ቀርበው እንደነበረ እና የተሰጡ አስተያየቶችን እርማት በማድረግ ዛሬ የመጨረሻው ረቂቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግምገማዊ ውይይት የሚደረግበት ይሆናል ሲሉ ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የቋንቋና ተጓዳኝ ትምህርቶች ስርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ዶ/ር አበበ ጋረደው እንዲሁም መደበኛ ያልሆኑና የህይወት ዘመን ትምህርት ፕሮግራሞች ዴስክ ኃላፊ አቶ ዘላለም አላጋው እንደገለፁት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ጥናትና ምርምር ተካሂዶ አዲስ የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶና ውይይት ከተካሄደ በኃላ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን በማስተባበር ለሀገር የሚጠቅሙና የነገውን ትውልድ በእውቀት የሚያንፁ መፅሐፎችን እያዘጋጁ መሆናቸውን ገልፀዋል:: ሁለቱም የስራ ኃላፊዎች ከዚህ ቀደም ያልተሞከረና አዲስ መንገድ በመከተል ለሀገር ውስጥ ምሁራንና ባለሙያዎች ዕድሉን መስጠት ችግሩን በቅርበት ስለሚረዱት የተሻሉ መፅሐፍትን ለማዘጋጀትና ችግሮቹን ለመቅረፍ፣ ባለሙያዎቹም ራሳቸውን እንዲያበቁበትና እንዲያዳብሩበት እንዲሁም ከዚህ በኃላ ለሚዘያጋጁት እንደመነሻ እንደሚሆናቸው፣ በሀገር በቀል እውቀት መስራት እንደሚቻል፣ ለባለሙያዎቻችንም እውቅና የሰጠንበት ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪንም ያስቀረ በመሆኑ ጠቀሜታው እንደሀገር የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርትና የት/አመራሮች የልዕቀት ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተከተል አዳነ በበኩላቸው እንደተናገሩት የዚህ መሰሉን የመማሪያ መፅሐፍት ለማዘጋጀት ከዚህ በፊት ልምዱ ባለመኖሩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም በርካታ ልምዶችን እና እውቀቶችን ያገኘንበት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ምሁራን ለትውልዱ የሚሰራ በመሆኑ ለሀገራችን፣ ለምሁራኖችና ባለሙያዎች ፋይዳው ብዙ ነው ብለዋል፡፡

ይህ የርቀት ትምህርት መማሪያ መፅሐፍት በመደበኛው ት/ት ክፍል ገብተው መማር ላልቻሉና ከስራቸው ጎን ለጎን ለሚማሩ የሚዘጋጅ በመሆኑ ግልፅና በሚገባ መልኩ መዘጋጀት እንዳለበት እንዲሁም በጋራ ግምገማዊ ውይይት ወቅት የት/ት ይዘቱን፣ ቋንቋውን፣ የት/ት ስርዓቱን እና ዲዛይኑን በጥንቃቄ በመፈተሽና አስፈላጊው አስተያየት ተሰጥቶበት በቀጣይ በተሰጡት ገንቢ አስተያየቶች መሰረት እርማት ተደርጎበት የመጨረሻው ረቂቅ ለት/ት ሚኒስቴር የሚላክ መሆኑን ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et