በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጀው የጎልማሶች ክህሎት ማበልፀጊያ ሞጁል የመጨረሻ ዙር ግምገማ ተካሄደ።
በኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ባለቤትነት እና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የአዲስ አበባ፤ የጂማና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ የተዘጋጀው የጎልማሶች ክህሎት ማበልፀጊያ የመማሪያ ሞጁል የመጨረሻ ዙር ግምገማ መድረክ በቢሾፍቱ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከሰኔ 18 - 20/2015 ዓም እየተካሄደ ነው፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ቴዎድሮስ ሽዋርገጥ በሞጁል ግምገማ መርሃግብሩ መክፈቻ ላይ ሲናገሩ የስርዓተ ትምህርት ቀረፃና የመማሪያ ሞጁሎች በአዲስ መልክ እንዲዘጋጁ የተፈለገበት ዋነኛው ዓላማ የህብረተሰቡን ነባራዊ ዕውቀት ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማወሀድ ነባር ዕውቀቶችን ከዘመናዊው ጋር በማቀናጀት የሀገር ውስጥ ምርቶችን በጥራትና በመጠን እንዲሻሻሉና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥራው ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል: ጊዜ: ጉልበትና እውቀት የሚጠይቅ መሆኑን ያስረዱት ዶ/ር ቴዎድሮስ ከአሁን ቀደም ተመሳሳይ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ስራዎች በውጭ ሀገር ባለሙያዎች በከፍተኛ ወጭ ሲሠሩ መቆየታቸውንና በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ምሁራን ስራው እንዲሸፈን መደረጉ በትምህርቱ ዘርፍ ሀገራችን የደረሰችበትን እምርታ አመላካች መሆኑን በመግለጽ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ይህን ዓይነት ግዙፍ ፕሮጄክት የማስተባባር ኃላፊነት በመቀበል በተፈለገው ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ በማድረግ ላይ ስለሚገኝ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር የመማሪያ ሞጁሎች በሀገር ውስጥ ምሁራን እንዲዘጋጁ መደረጉ ለውጭ ባለሙያዎች የሚከፈለውን ከፍተኛ ወጭ ከማስቀረትም በላይ የሀገሪችን ባህልና ወግ ተጠብቆ የዓለም ወቅታዊ ትኩረቶችን ባገናዘበ መልኩ ዜጎቻችን እንዲማሩ የሚያግዝ በመሆኑ በትምህርት አቀባበል ላይም የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ብሎ ባቋቋመው ዘመናዊ የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከል አስተባባሪነት ለአንድ ዓመት ሲካሄድ የቆየው ይሄው የመማሪያ ሞጁሎች ዝግጅት በማጠናቀቅያ ምዕራፍ ላይ መድረሱንና በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት እንዲተቹትና አስፈላጊውን የማሻሻያ ግብዓት እንዲሰጡበት ይህ የግምገማ መድረክ መዘጋጀቱን የጠቆሙት ዶ/ር አያኖ ሥራው እንደተጠናቀቀ ለትምህርት ሚኒስቴር በማስረከብ ለየክልሎች የሚደርስ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሥርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያና የትምህርት አመራር ልህቀት ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተከተል አዳነ በዚሁ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ በሶስት የትምህርት መዋቅሮች በመዘጋጀት ላይ የሚገኙት እነዚህ ሞጁሎች የቅድመ መደበኛ፡ የርቀት ትምህርትና የጎልማሶች ትምህርት ላይ ያተኮሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግምገማ እየተደረገባቸው የሚገኘው እነዚህ ሞጁሎች ከ230 በላይ የትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎችና የቴክንክና ሙያ ኮሌጆች የተሳተፉበት ሲሆን በ7 የተለያዩ መስኮች የተመደቡ 23 የተመረጡ የሙያ ዘርፎች: ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ባገናዘበ መልኩ የትምህርት ሞጁል የተዘጋጀላቸው መሆኑን አቶ ተከተል አስረድተዋል፡፡
ለሶስት ቀናት በሚካሄደው በዚህ የትምህርት ሞጁሎች ግምገማ መድረክ ከሐዋሳ: ጅማ: ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች: ከትምህርት ሚኒስቴር: እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ማዕከላት የተወጣጡ ከ300 የሚበልጡ ባለሙያዎች መሳተፋቸው ታውቋል::