የህዝብ ተወካዮች ቋሚ ኮሚቴ ጉብኝት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ

የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰዉ ኃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመስክ ምልከታ አካሄዱ።

በተከበሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የተመራው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰዉ ኃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሁለት ቀናት የመስክ ምልከታ ከግንቦት 29 - 30/2015 ዓም ያካሄዱ ሲሆን በተለያዩ ካምፓሶች የሚገኙ መሰረተ ልማቶችንና አገልግሎት ሰጪ ክፍሎችን ጎብኝተዋል::

በጉብኝታቸው መጀመርያ ላይ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር ጋር ስለ ጉብኝቱ ዓላማ የዳሰሳ መስፈርቶች አጠር ያለ ገለፃ የተደረገ ሲሆን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፕላንና ተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ቡርቃ ጠቅለል ያለ ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አቅርበዋል::

የቋሚ ኮሚቴዉ ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ እንደተናገሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገራችን የተማረ የሰዉ ኃይልን በማፍራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ እንደመሆኑ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም ከመጀመሪያው ትዉልድ ዩኒቨርሲቲዎች በቅርቡ ለምርምር ዩኒቨርሲቲነት እንደተለየ አውስተው ስለሆነም ዩኒቨርሲቲው በውስጥ አደረጃጀትም ሆነ በመሰረተ ልማት ግንባታው እንዲሁም ለትምህርትና አገልግሎት ጥራት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በማሟላት ረገድ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ መዳሰስ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል::

የአካል ጉብኝቱ በዋናው ግቢ: በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት: በግብርና ኮሌጅ: በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እንዲሁም በወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ባሉ የተለያዩ ክፍሎች የተከናወነ ሲሆን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከመስክ ምልከታቸው ባሻገር የአካዳሚክና የአስተዳደር ሰራተኞችና አመራሮችን እንዲሁም ተማሪዎችን አወያይተዋል:: በውይይቱ በርካታ ጠቃሚ ግብዓቶችን ማግኘት እንደቻሉና ባዩት ነገር ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል::

በውይይቱ ወቅት ከተነሱ ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝነት: የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር: የመውጫ ፈተና: የበጀት ጉዳይ: የተደራጁ ቤተ ሙከራዎች አስፈላጊነት: የትምህርት ጥራት: ተከታታይና ስርፀት የሌላቸው የትምህርት ሪፎርም ሥራዎች: ዓለም አቀፋዊነትና የምርምር ህትመት ጥራት በተለይም ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም: የማካካሻ (ሬሜድያል) ትምህርት ጉዳይ: የ12ኛ ክፍል ፈተና: የመምህራን የኑሮ ሁኔታና ያልተመጣጠነው የዋጋ ግሽበት ከተጨማሪው የቤት ክራይ ክፍያ ጋር አለመገናኘት: ውስብስብና አስቸጋሪ የግዥ ሥርዓት መኖር: የቤተ ሙከራ ግብዓት አቅርቦት ውስንነት ይገኙበታል::

የተከበሩ ዶክተር ነገሪ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዉ በሀገራችን ካሉ ስመጥሩ የትምህርት ተቋማት አንዱ እንደመሆኑ ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንፃር፣ ጥራትና ብቃት ያለው የሰዉ ኃይል ከማፍራትና ራስ-ገዝ ከመሆን ጋር ተያይዞ ምን እየሰራ እንደሚገኝ፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ መፍትሄዎችን በውይይትም በአካላዊ ምልከታም መዳሰሳቸውን ገልፀዉ ዩኒቨርሲቲው ለስሙ የሚመጥን ይዞታ ላይ እንዳለ ለማታዘብ መቻላቸውንና ባዩት ነገር ተስፋ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል። አክለውም የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተግባራት ሕግን ተወያይቶ የማዉጣት፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የፓርላሜንተሪ ዲፕሎማሲ እንዲሁም የሕዝብ ዉክልና ስራዎችን እንደሆኑ ጠቅሰው ወደፊት የተሻለ ሥራ እንደሚሰራም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል ።

የቋሚ ኮሚቴዉ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ፍሬዉ ተስፋዬ በበኩላቸው በሀገራችን በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቅሰው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የሚያስችለውን ሥራ ከሰዉ ኃይል ዝግጅት፣ አደረጃጀትና ሌሎች አንኳር ተግባራት አንፃር ምን እንደሚመስል፣ በአለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪነታቸዉን ከፍ ለማድረግ በምርምር፣ የተማሪ ልዉዉጥና ከአጋር አካላት ጋር ተቀራርቦ ከመስራት አንፃር ምን እየተከናወነ እንደሆነ፣ ከዩኒቨርስቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር አኳያ ዩኒቨርስቲው ያለዉ ልምድ፣ የዩኒቨርስቲ መዉጫ ፈተናን በተመለከተ የተማሪዎቹ የስነ ልቦና ዝግጅት ምን እንደሚመስልና በቀጣይ ምን ይጠበቃል በሚሉ ነጥቦች ላይ ውይይት ማድረግና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ጉብኝታቸው ወሳኝ እንደሆነ አብራርተዋል።

በተቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረትም በዩኒቨርሲቲዉ በተተገበሩ እና እየተከናወኑ ባሉ ዝግጅቶች ላይ ዉይይት የተካሄደ ሲሆን ክፍተቶች በታዩባቸዉም ላይ እርምት እንዲወሰድባቸዉ አስተያየትና አቅጣጫ ከተቀመጠ በኃላ ምላሽ ባላገኙ ነጥቦች ላይ ደግሞ በቀጣይ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ተገልፆ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et