የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሲያደራጅ የቆየው የ Advanced Trauma Life Support (ATLS) ማሰልጠኛ አለምዓቀፍ እውቅና ተሰጠው፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከኤ. ሲ. ኤስ (American College of Surgeons) ጋር በመተባበር በሃገራችን በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነ "Advanced Trauma Life Support /ATLS" የተሰኘ አደጋ የደረሰባቸዉን ሰዎች እንዴት ማከምና ማዳን እንደሚገባ በተግባር የታገዘ ከፍተኛ ስልጠና የሚሰጥ ማዕከል ያደራጀ ሲሆን የዚህ ዓይነቱን ስልጠና ለመስጠት ከኢትዮጵያ የመጀመሪያው ከአፍሪካ ደግሞ አራተኛው በመሆን በ American College of Surgeons Committee on Trauma አለምዓቀፍ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡
የኮሌጁ የክህሎት ማሰልጠኛ ላቦራቶሪ ማናጀርና የኮርሱ አስተባባሪ ረ/ፕሮፌሰር ኤፍሬም ጌጃ እንደገለፁት ይሄንን ስልጠና እውን ለማድረግ ላለፉት ሦስት ዓመታት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንና ለስልጠናው የሚያስፈልጉትን ዳይሬክተር፣ ምክትል ዳይሬክተርና አሰልጣኞችን በማሰልጠን እንዲሁም የቤተሙከራውን ግብዓቶች አለምዓቀፍ ስታንዳርድ ያሟላ መሆኑን በማረጋገጡ ስራ አሜሪካን ኮሌጅ ኦፍ ሰርጅንስ (American College Of Surgeons) “Operation Giving Back” በተሰኘው መርሃ ግብሩ በኩል ድጋፍ አድርጓል፡፡ በዚህም ዶ/ር እምነት ተስፋዬ በዳይሬክተርነት እና ዶ/ር ቴዎድሮስ ታደሰ በረዳት ዳይሬክተርነት ወደ ቱርክና የተባበሩት ኤምሬትስ በመሄድ አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ እንደ ስተባባሪው ገለጻ የዚህ አይነቱ ስልጠና በአፍሪካ ደረጃ ከአሁን በፊት በሦስት ሀገራት ማለትም በደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ እና ኬኒያ ላይ ብቻ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ስፔሻሊስት ሀኪሞቻችን ወደ እነዚህ ሀገራት በመሄድ ለስልጠናው ብቻ ከ40 ሺህ ብር በላይ እከፈሉ ሲሰለጥኑ እንደነበረና አሁን ግን በኮሌጃችን በተመጣጣኝ ክፍያ አልፎም ስፖንሰር ሲያገኙ በነፃ እንዲሰለጥኑ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የክህሎት ማሰልጠኛ ቤተሙከራ ማቋቋም ችለናል ብለዋል፡፡
የኮሌጁ ክህሎት ማሰልጠኛ ቤተ ሙከራ (skill lab) አለም ዓቀፍ ደረጃን እንዲያሟላ ለማድረግ በሚሰራበት ወቅት ግብዓቶችን በማቅረብና ቤተሙከራውን በማደራጀት፣ አንድ ዙር የአሰልጣኞች ስልጠናና ሁለት ዙር የሃኪሞች ስልጠና (Provider course) በመስጠት፣ አሰልጣኞችን ከአሜሪካ፣ ግብጽና ሊባኖስ ስፖንሰር አድርጎ በማምጣት እንዲሁም American College of Surgeons Committee on Trauma ቦታው ላይ ተገኝቶ ሙያዊ ምልከታና ግምገማ በማድረግ ፍቃድ የመስጠቱን ስራ አሜሪካን ኮሌጅ ኦፍ ሰርጅንስ (American College of Surgeons Operation Giving Back) ያከናወነ ሲሆን የፌደራል ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ሰልጣኞችን ስፖንሰር በማድረግ ትብብር አድርጓል፡፡ ከዚህ ሁሉ ስራ በኋላ አሁን አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የክህሎት ማሰልጠኛ ቤተሙከራ ማደራጀትና በአሜሪካው ተቋም ግምገማ መሰረት የሚጠበቅብንን ሁሉ ስላሟላን ይህ ስልጠና በኮሌጃችን እንዲሰጥ በአፍሪካ ካሉት አራተኛው ከኢትዮጵያ ደግሞ የመጀመሪያው ማዕከል ሆኖ ፍቃድ ማግኘት እንደተቻለና የስምምነት ሰነድ እንደተፈራረሙ ተናግረዋል ።
በማጠቃለያውም አሁን በኮሌጃች ከአሜሪካ፣ ከግብፅና ከሊባኖስ በተውጣጡ አስራ ሁለት ያህል ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሞያዎች የተሰጠው Advanced Trauma Life Support (ATLS) ስልጠና የመጀመሪያው ሲሆን ወደፊት ከጤና ሚኒስቴርና ኤ ሲ ኤስ ጋር በመተባበር ሌሎች የሰዉ ህይወትን ቶሎ ለማዳን የሚያግዙ ስልጠናዎችን ለሀኪሞችና ሌሎች የህክምና ባለሞያዎች ለመስጠት እቅድ ይዘናል ያሉ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሆስፒታሎች የሚሰሩ ስፔሻሊስት ሀኪሞችን በመቀበልም ይሄንን አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች እንዴት ማከም እና ማዳን እንደሚገባ በክፍል ውስጥ በሚሰጥ ዕውቀት እንዲሁም በተግባር ልምምድ የታገዘና የብቃት መመዘኛዎችን ማለፍ የሚጠይቅ በጠንካራ ሲስተም የታገዘ ስልጠና ለመስጠት ብቁ ሆነናል ብለዋል፡፡
በዚህ የትብብር መርሃግብር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመጀመርያው ዙር ከተለያዩ ሆስፒታሎች የተወጣጡ 16 ስፔሻሊስት ሀኪሞችንና በ2ኛው ዙር 13 ስፔሻሊስት ሀኪሞችን አስመርቆ በድጋሚ ከሰልጣኞች መካከል የተመረጡ 9 ሰልጣኞች የአሰልጣኞች ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡በተጨማሪም ይሄንን ስልጠና ወስደው የብቃት ማረጋገጫውን የተግባር ፈተና በብቃት ለሚያልፉ ምሩቃን ለአራት ዓመታት የሚቆይ አለምዓቀፍ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ሰርተፊኬት) እንደሚሰጣቸው ተገልጽዋል፡፡
