የጥራት ማረጋገጫና ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት የጥራት ግኝት ሪፖርት ላይ ውይይት አካሄደ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጥራት ማረጋገጫና ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት በኮሌጅ ደረጃ በሚገኙ የትምህርት ክፍሎች የጥራት ግኝት ሪፖርት ላይ የካቲት 10/2015ዓ.ም ውይይትና ግምገማ አካሄደ፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በመክፈቻው ላይ እንደተናገሩት ጥራት የሁሉም ነገሮች መሰረት እንደመሆኑ እኛም ከትኩረት መስኮቻችን አንዱ ጥራትን በማድረግ ጥራትና ብቃት ያላቸውን ምሩቃንን ለማፍራት እና ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለመስራት እንዲሁም ለህብረተሰባችንም ተደራሽ ለማድረግ ጥራት ላይ በርትተን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ አክለውም ከዚህ በኃላ የተማሪዎች ምርጫ ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞች ተመራጭ እንዲሆኑ የትምህርት ክፍሎችና ኮሌጆች ተናበውና ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ገልፀው በሀገር ደረጃም የጥራት መመዘኛው ነጥሮ እየወጣ በመሆኑ እንደዩኒቨርሲቲም ተወዳዳሪና ተመራጭ ለመሆን ጥራት ላይ ተረዳድተን መስራት የሚኖርብን ሲሆን በዚህ ፕሮግራምም እስካሁን የተሰሩትን በመገምገምና ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት ጥራት ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የጥራት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ተባባሪ ዳይሬክተር ወ/ሮ መቅደስ መኮንን እንደተናገሩት የፕሮግራም ኦዲት ግኝት በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በዚህ ፕሮግራም ከዚህ በፊት የከፍተኛ ት/ት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ በአሁኑ አጠራር ደግሞ የኢትዮጵያ ስልጠና ባለስልጣን ባወጣው መስፈርት መሰረት የትምህርት ክፍሎችን በመገምገም የውስጥ ግኝት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በፕሮግራሙ የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተለይተውና የማሻሻያ መተግበሪያም የቀረቡ ሲሆን በቀጣይ የማሻሻያ መተግበሪያውን ተግባራዊ በማድረግና በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦችን በመውሰድ ለቀጣይ ውጫዊ ግምገማ ትምህርት ክፍሎች ራሳቸውን ዝግጁ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡