የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ለሩሙዳሞ ራማ ትምህርት ቤት የፀሐይ ብርሃን ኃይል መሰብሰቢያ (ሶላር) መሳሪያ ገጠማና ተከላ አደረገ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም ከኮሪያ ዮክ ካምፓኒ እና ከአቶ ሙሉጌታ ሙንጣሻ የቡና አቅራቢ የግል ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን በሲዳማ ክልል አርቤጎና ወረዳ ለሩሙዳሞ ራማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፀሐይ ብርሃን ኃይል መሰብሰቢያ (ሶላር) መሳሪያ ገጠማና ተከላ አድርጓል፡፡
የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ም/አካዳሚክ ዲን ዶ/ር ሽመልስ ንጋቱ እንደተናገሩት ይህ የፀሐይ ብርሃን ኃይል መሰብሰቢያ (ሶላር) መሳሪያ በዚህ ትምህርት ቤት ሲተከል ሁለት ዓላማን ለማሳካት ታስቦ መሆኑ ታውቋል፡፡ የመጀመሪያ ዓላማ በትምህርት ቤቱ ለሚማሩ 250 ተማሪዎች በዚህ በተገጠመው መሳሪያ ቻርጅ የሚደረግ መሳሪያ የሚታደል በመሆኑ ሁልጊዜ ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ ይህንን መሳርያ ይዘው በመምጣት ቻርጅ አድርገው ወደቤታቸው ሲሄዱ የአምፖል ብርሃን እንዲያገኙና ትምህርታቸውን እንዲያጠኑ እንዲረዳቸው እና ቻርጀሩ ሞባይላቸውንም ቻርጅ እንዲያደርጉበት ሲሆን ሁለተኛው ዓላማ ተማሪዎች ይህንን አገልግሎት ለማግኘት ሲመጡ ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ እንዲማሩም እንደሚረዳቸው ዶ/ር ሽመልስ ተናግረው የዚህ መሰል መሳሪያ ገጠማና ዝርጋታ በቀጣይም ለሁለት ትምህርት ቤቶች እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የአቶ ሙሉጌታ ሙንጣሻ የቡና አቅራቢ የግል ድርጅት ተወካይ ወጣት ድጋፉ ሙሉጌታ በበኩሉ የዚህ መሰሉ ድጋፍ ለመንግስትና እንደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ላሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚተው ሳይሆን በአካባቢው ያሉ የግል ባለሀብቶችም ትምህርት ቤቶችን በመደገፍና የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ በመደገፍ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው የሩሙዳሞ ራማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ኃላፊዎችና የተማሪ ወላጆችም በተደረገላቸው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን ከሰጡት አስተያየት ለማወቅ ተችሏል፡፡