የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በመንፈቅ አመቱ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ግምገማ አካሄደ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የም/ቴ/ሽ/ም/ፕ/ጽ/ቤት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ ዩኒቨርሲቲው ከሶስት አመታት ወዲህ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ለመውጣት ለምርምሩ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አክለውም ዛሬ የሚካሄደው ግምገማ በዩኒቨርሲቲው ስር የሚገኙ አምስት ኮሌጆች ላለፉት ስድስት ወራት የሰሯቸውን የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ያሉበትን ደረጃ እንዲሁም የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች በዝርዝር የሚያቀርቡበት መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው በአምስት ዘርፎች በግብርና፣ በጤና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በሶሻል ሳይንስና ሁማኒቲስ እና በትምህርት ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እንዲሁም ወደ ስፔሻሊቲ ማዕከልነት ለመሸጋገርና በሕብረተሰቡ ብሎም የምርትና የአገልግሎት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በሳይንሳዊ መንገድ በመቅረፍ እንደ ሀገር ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ ለማፋጠን እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በዚህ ረገድ ምርምሮች በዋናነት አራት ነገሮችን እንዲያሟሉ ይኸውም አግባብነት እንዲኖራቸው፣ጥራታቸውን የጠበቁ፣ አሳታፊ እና ተደራሽ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተናቦ መስራት ይገባል ብለዋል።
የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ም/ቴ/ሽ/ጽ/ቤት ምክትል ዲንን ወክለው የተገኙት አቶ ሙሉጌታ በቀለ በበኩላቸው ኮሌጃቸው በየጊዜዉ በሚሰሯቸው ምርምሮች ምን ያህል የማህበረሰቡ ችግሮችን መፍታት ተችሏል ብሎ መጠየቅ እንደሚገባ እና የምርምር ስራዎች በመጀመሪያ አንገብጋቢ የሆኑ የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች ተደራሽ በማድረግ ለይ ትኩረታቸውን ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል። ሲያክሉም በዚህ ስድስት ወር ውስጥ በየኮሌጁ በዘርፉ የተሰሩ ስራዎች ያሉበትን ደረጃ በመለየት በተቀሩት ስድስት ወራት የተሻለ ስራን ለመስራት የልምድ ልውውጥ ለማካሄድ የዛሬው ግምገማ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
በዕለቱ የግብርና፣ ጤና ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የተፈጥሮና ኮምፒቲሽናል ሳይንስ እና የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች የመንፈቅ አመት ሪፖርታቸውን አቅርበው በቀረበው ሪፖርት ላይ ግምገማ ተካሂዷል።