በዘላቂ የደን አያያዝና የተፋሰስ ጥበቃ የምርምር ሥራዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመመካከር የሚያስችል አውደ-ጥናት ተካሄደ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ በወንዶ ገነት አካባቢ በሚገኙ አነስተኛ ተፋሰሶች ዙሪያ በዘላቂ የደን አያያዝና የተፋሰስ ጥበቃ የምርምር ሥራዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመመካከር የሚያስችል አውደ-ጥናት ታህሳስ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዳይሬክተር ጀነራል ክቡር አቶ ከበደ ይማም የደን ዘርፍ ለሀገራችን የዕድገት ምጣኔ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ ከማበርከቱም በላይ የስራ ዕድል በመፍጠር፣ የማገዶ ፍጆታን በማሟላት፣ የብዛ-ሕይወትን በመጠበቅ፣ የተቃጠለ በካይ ጋዝን በማመቅ፣ የአፈር ብክለትን በመከላከል እና ዘላቂ የውሃ ፍሰትን በመጠበቅ እንዲሁም ሌሎች የስነ-ምዕዳር አገልግሎቶችን በመስጠት የማይናቅ ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡ አክለውም እንዳሉት ይህ ውስን የደን ሃብት በእርሻ መሬት መስፋፋት፣ ዕቅድ ላይ ባልተመሰረተ የማገዶ አጠቃቀም፣ በሕገ-ወጥ የጣውላ ምርቶች መንስኤና ምክንያቶች በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆኑን ገልፀው ሳይንሳዊ ያልሆነ የደን አጠቃቀምና በዘርፉ ብቁ የሆኑ የደን ስርፀት ባለሙያዎች ባለመኖራቸው በደኑ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን መቀነስ ብሎም መቀልበስ እንዳይቻል አድርጎታል፡፡
የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሳሙኤል በቀለ ኮሌጁ በፕሮጀክቱ አማካኝነት ዘርፈ ብዙ ምርምርና ጥናት በማካሄድ በጥናቱ ውጤት ላይ በመመርኮዝም የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለደን ባለሙያዎች በመስጠት በርካታ ስራዎችን ያከናወነ መሆኑን ገልፀ በዛሬው አውደ ጥናትም ባለፉት ሁለት ዓመታት በወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዙሪያ ተግባር ተኮር ተሳትፏዊ ዘላቂ የደን አያያዝና የተፋሰስ ጥበቃ የምርምር ስራዎችን ለመገምገምና የባለድርሻ አካላት ሚናን በመለየት የወደፊት አቅጣጫን ለማስቀመጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በወ/ገ/ደ/ተ/ሀ/ኮሌጅ ተመራማሪና የ IS-CFSDP ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር መሰለ ነጋሽ የ IS-CFSDP ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ የደን ልማትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በስውዲን መንግስት ገንዘብ ድጋፍ በወንዶ ገነት ተፋሰስ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የግጭት አፈታት፣ የወንዶ ገነት ተፋሰስ የስነ-ምህዳር አገልግሎት አቅም እና የቱሪዝም አቅም ላይ ያተኮሩ ሶስት ጥናቶችን በባለሙያዎች ማስጠናቱን ታውቋል፡፡ በማከልም የእነዚህ ጥናቶች ውጤትን ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለማሳወቅና በተፈጥሮ ሀብት ዘላቂያዊ ጥበቃና ልማት ዙሪያ ምክክር በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ምክረ ሃሳብ ለማግኘትና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአውደ ጥናቱም የምርምርና ጥናት ውጤቶቹ ቀርበው ከባለድርሻ አካላት ጋርም ውይይት ከተካሄደ በኃላ በቀጣይ ስራዎች ላይ የጋራ መግባባት በመድረስ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡