የወንዶገነት ደንና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ በመውጫ ፈተና ዙሪያ ሥልጠና ሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶገነት ደንና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ የመውጫ ፈተናን አስመልክቶ ታህሣሥ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ለመምህራንና በየደረጃው ለሚገኙ የኮሌጁ ሥራ ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ሳሙኤል በቀለ በዚሁ ወቅት ሥልጠናው የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያን መሠረት ባደረገ መልኩ መምህራና ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የመውጫ ፈተና ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ከምንጊዜውም በተሻለ መልኩ ተማሪዎችን ለማብቃትና የሥነ-ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ ለማስቻል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አክለውም የመውጫ ፈተናው መኖር በሀገር ደረጃ የትምህርትን ጥራት ለማሻሻል እየተደረገ ያለውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የገለጹት ዶ/ር ሳሙኤል ለስኬታማነቱ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዋናው ግቢ የሳይኮሎጅ ትምህርት ክፍል መምህራን የሆኑት ዶ/ር ደርቤ ወርቅነህና ዕጩ ዶ/ር ሀብተማሪያም ካሣ አማካይነት ሥልጠናው ተሰጥቷል፡፡
በቀጣይም በሁሉም ኮሌጆች ለሚማሩ ተመራቂ ተማሪዎች የፈተናውን ዓላማና አስፈላጊነት በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እንደሚዘጋጁ ተገልጾአል፡፡