በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረዉን አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀንን “ሙስናን መታገል በተግባር” በሚል መሪ ቃል ህዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም አከብሯል።
የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ኢንጂነር ፋሲካ ቤተ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ስናነሳ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከራሳቸዉ ያርቁታል፤ ሙስናና ብልሹ አሰራር መጠኑ እና አይነቱ ይለያይ እንጂ በሁሉም ተግባር ዉስጥ ይገኛል ብለዋል። አክለዉም ሙስና ከግለሰብ አንስቶ በሀገር ደረጃ ከባድ ጉዳት እንደሚያደርስ ገልፀዉ ይህንን አፀያፊ ተግባር ለማስተካከል በንደፈ ሃሳብ ከማወቅ በዘለለ በተግባር ልንታገለዉ ይገባል በማለት እንደ ተቋምም የተሰጠንን ተልዕኮ ለመወጣት መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እና ኃላፊዎች ጊዜያችንን፣ ሀብታችንን እና እዉቀታችንን ለታሰበለት ዓላማ በማዋል ሙስናንና ብልሹ አሰራርን የሚፀየፍ ብቁ ዜጋ በየዘርፋችን ልናፈራ ይገባናል ብለዋል።
በዕለቱም በህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ መምህር የሆኑት አቶ አዱኛ ስሜ ሙስና፣ መንስሔዎቹና መፍትሄዎቹ በሚል የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ተሳታፊዎችም በቀረበዉ ርዕስ ላይ ዉይይትና ተሳትፎ በማድረግ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።