የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ በ2014ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀምና በ2015 ዓ.ም ዕቅድ አዘገጃጀት ላይ ውይይት አካሄደ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ በ2014ዓ.ም የኮሌጁ ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2015 ዓ.ም ዕቅድ አዘገጃጀት ላይ ነሐሴ26 ቀን 2014 ዓ.ም ግምገማና ውይይት አካሂዷል፡፡
የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዳኜ ሽብሩ ሲናገሩ ኮሌጃችን ከመማር ማስተማር፣ ከምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በእውቀት፣ በአስተሳሰብና አመለካከት ላይ እየሰራና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይም ግንዛቤ የመፍጠርና ማሳደግ፣ የተለያዩ ምሁራንን ከተለያዩ ቦታዎች በመጋበዝ ስለ ሰላም አስፈላጊነት፣ በጦርነቱ ወቅትም በተለይ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ወታደሮችና የጤና ባለሙያዎችን ከስነ-ልቦና ጋር በተያያዘ ስልጠና የመስጠት እንዲሁም በሶሻል ሚዲያ እና በዜና አውታሮች የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን እንዴት መለየትና መከላከል እንደሚቻል፣ የኮሌጃችን ምሁራንም በተለያዩ ሚዲያዎች በመጋበዝ ለማህበረሰቡ ሃሳቦችን በማካፈል እና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ እንደ ኮሌጅ በ2014ዓ.ም በርካታ ስራዎች ሲሰራ የቆየ ቢሆንም አፈፃፀማችንን በመፈተሽና ድክመቶቻችንን ነቅሰን በማውጣት በቀጣይ እንዳይደገሙ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
ዲኑ አክለውም በዚህ ውይይት ዩኒቨርሲቲያችን የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብሎ እንደመለየቱ የዩኒቨርሲቲው አዲሱ የ2015 ዓ.ም መሪ ዕቅድ ምን እንደሚመስል በመፈተሽ ኮሌጃችንም የራሱን ዕቅድ እንዴት ማዘጋጀት እንዳለበት፣ በ2015 ዓ.ም በሚጀመረው የመውጫ ፈተና አዘገጃጀት ላይ፣ በቀጣይ የ12 ክፍል ተማሪዎች የማጠናቀቂያ ፈተና የሚወስዱ በመሆኑ ፈታኝ መምህራን፣ ለዓይነ-ስውራን አንባቢ እና ቆጣሪ መምህራንን ምልመላ ማድረግ፣ አዳዲስ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከዩኒቨርሲቲው የመጡ ወይም የተሻሻሉ ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ እና የ2015ዓ.ም በጀትን በማሳወቅና አጠቃቀም ላይ በሰፊው ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የፕላን እና ተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ቡርቃ የዩኒቨርሲቲው አዲሱን የ2015ዓ.ም መሪ ዕቅድን ሲያቀርቡ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በተልዕኮ ልየታ መሰረት ከምርምር ዩኒቨርሲቲ አንዱ እንደመሆኑ የትምህርት ሚኒስቴር የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እና መለኪያና መመዘኛዎቹንም በመዘርዘር አዲስ ዕቅድ የላከልን በመሆኑ ከዚያ በመነሳት አዲስ መሪ ዕቅድ መዘጋጀቱን እና የትኩረት አቅጣጫዎቹም ሳይሸራረፉ መወሰዳቸውን አብራርተው ኮሌጆችም ከዚህ በመነሳት ማቀድ እንዳለባቸው እንዲሁም ወደፊትም የዩኒቨርሲቲውም ሆነ የኮሌጆች አፈፃፀም የሚገመገመው በተቀመጡት መመዘኛዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በፕሮግራሙም በኮሌጁ ዲን የተነሱ ነጥቦች ላይ ግምገማና ውይይት ተደርጎባቸው በታዩ ደካማና ጠንካራ ጎኖች ላይ በተሳታፊዎች አስተያየት ተስጥቶባቸው ፕሮግራሙ መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡