በኖራ ድንጋይ ላይ እየተደረገ ያለው ጥናት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ሀዩ አስታወቀ

በሲዳማ ክልል በኖራ ድንጋይ ላይ እየተደረገ ያለው ጥናት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

በውይይት መክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ እንደገለጹት የሰብል ምርት፣ የእንስሳት እርባታና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኩረት መስኮች ናቸው፡፡ በዚህም ዩኒቨርሲቲው የግብርና ምርታማነት፣ የአፈር፣ የውሃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩ የጥናት ውጤቶችን መሰረት ያደረጉ የማ/ብ አገልግሎቶችን ለአካባቢው ማህበረሰብ ሲያበረክት መቆየቱን አውስተዋል፡፡ ዶ/ር ታፈሰ አክለውም በሲዳማ ክልል ካለው ደጋማ አካባቢ 20 በመቶው አፈር በአሲዳማነት የተጠቃ በመሆኑ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከጉራጌ ዞን ድረስ ኖራ በማምጣት እንዲሁም አሲዳማነትን የሚቋቋሙ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶአደሮች በማቅረብ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የሄኛውን ጥናት ለማድረግ የተነሳውም ያለውን ከፍተኛ የአፈር አሲዳማነት ለመቆጣጠር የተሻለ አማራጭ ለማግኘት አስቦ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሄንን አንገብጋቢ የህዝብ ችግር ለመፍታት የሚያስችል ሳይንሳዊ ጥናት ላደረገው የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተመራማሪዎች ቡድንም ለዚህ ውጤት በመድረሳቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለው ውይይቱን አስጀምረዋል፡፡   

በሲዳማ ክልል የአፈር አሲዳማነትን በኖራ በማከም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳል የተባለለት የኖራ ድንጋይ አሰሳ ጥናት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማራማሪዎች  እየተሰራበት የቆየ ሲሆን የጥናቱ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ውይይትና ምክክር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ተካሂዷል፡፡

የምርምር ቡድኑ መሪና የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የዩኒቨርሲቲ- ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ባዩ ቡንኩራ የጥናታቸውን ግኝት ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ጥናቱ በሲዳማ ክልል ውስጥ የኖራ ድንጋይ ያለበትን አካባቢ ለመለየት ታስቦ በሁሉም ወረዳዎች ላይ የተደረገ ሳይንሳዊ ጥናት ሲሆን የመጀመሪያው ዙር የጥናቱ ውጤትም መሰረት በክልሉ የኖራ ድንጋይ ያለባቸው ቦታዎችን ልየታ ማድረግ የተቻለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ባዩ  በንግግራቸው ጥናቱ ሙሉ በሙሉ ያላለቀ መሆኑን ገልጸው የጥናቱን ውጤትም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር በቀጣይ ሊሰሩ የሚገባቸው በርካታ ቀሪ የቤት ስራዎች እንዳሉ አሳውቀዋል፡፡ ከእነዚህ ቀሪ ስራዎች መካከልም የተጠቀሱት ከኖራ ድንጋይ ኖራን በፋብሪካ በማምረት በክልሉ በአፈር አሲዳማነት ምክንያት እየተቸገሩ ያሉትን ባርካታ አርሶአደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ተመራማሪዎች እና ከሲዳማ ክልል ግብርና ቢሮ እንዲሁም ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የግብርና ጽ/ቤት ባለሙያዎች ተገኝተው በቀረበው ጥናት ውጤት ላይ ውይይትና ምክክር ያደረጉ ሲሆን በቀጣይም ጥናቱ ዳብሮና በፋብሪካ ደረጃ ኖራ ተመርቶ ለተጠቃሚዎች የሚደርስበት ቀጣይ ስራዎች እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et