በአርቤጎና ወረዳ እየተሰራ ያለውን የዶሮ ዕርባታ በባለድርሻ አካላት ተጎበኘ

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በአርቤጎና ወረዳ እየተሰራ ያለውን የዶሮ ዕርባታ ለባለድርሻ አካላት አስጎበኘ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴ/ሽ/ም/ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት በማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አማካኝነት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በተለያዩ ዘርፎች እያከናወነ ሲሆን በሲዳማ ክልል አርቤጎና ወረዳ ከከፍተኛ ተቋማት ተመርቀው ስራ አጥ የነበሩ ወጣቶች ተደራጅተው በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ የአንድ ቀን ጫጩቶች እንዲወስዱ ተደርጎ በማሳደግና በማርባት እየሰሩ ያለውን የዶሮ ዕርባታ ለባለድርሻ አካላት ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም አስጎብኝቷል፡፡

የምርምርና ቴ/ሽ/ም/ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር መብራቱ ሙላቱ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችን፣ ስራ አጥ ወጣቶችን እና ሴቶችን፣ መምህራንን እና የትምህርት ባለሙያዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በስድስት በተመረጡ ዘርፎች ማለትም በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በጤናና ስነ-ምግብ እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን፣ የእንስሳት እና ሰብል ዝርያዎችን በሳይንሳዊ መንገድ በማሰራጨትና በማላመድ፣ ቴክኖሎጂን በማሸጋገር፣ ስልጠናና የማማከር አገልግሎት በመስጠት የአካባቢው ማህበረሰብ ኑሮ እንዲሻሻል በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዶ/ር መብራቱ አክለውም ጉብኝቱ ከዚህ ቀደም በአርቤጎና ወረዳ ከከፍተኛ ተቋማት ተመርቀው ስራ አጥ የነበሩ ወጣቶች ተደራጅተው በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ የአንድ ቀን ጫጩቶች እና ለዶሮ ዕርባታ የሚያስፈልጉ ግብአቶች እንዲወስዱ ተደርጎ በማሳደግና በማርባት እየሰሩ ያለውን የዶሮ ዕርባታ ለመመልከትና ያሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመገምገም ሌሎች አርሶ አደሮችም ከዚህ ተሞክሮ እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአርቤጎና ወረዳ አስተዳደር ተወካይ የሆኑት አቶ ኖጦራ ታየ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት የተሻሻሉ የገብስ ዝርያዎች፣ የቦንጋ በጎችን፣ ለእንስሳት መኖ የሚሆን ዲንሾ ሳርን፣ የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን በወረዳው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን ለወጣቶችም የስራ ዕድልን ከማመቻቸት በዘለለ በቅርቡም በዓሳ ማርባት ላይ እንድንሰራ በርካታ ድጋፎችን እያደረገልን በመሆኑ እያመሰገንኩኝ በቀጣይም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቁን እንዲቀጥል አደራ እላለሁኝ ብለዋል፡፡

በዕለቱም ግብኝት ከተደረገ በኃላ ወጣት ስራ ፈጣሪዎቹ ከተበረከተላቸው የዶሮ ጫጩቶች በተጨማሪ የዶሮ ዕርባታው በተፈለገው መልኩ እንዲቀጥል በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች እየተደረገላቸው ያለው ሙያዊ ድጋፍ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማስቻሉን ገልፀዋል፡፡

 

 

 

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et