የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ለጎልማሶች ትምህርት አመቻቾች ስልጠና ሰጠ፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴ/ሽ/ም/ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት በማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አማካኝነት በሲዳማ ክልል ከሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የመሰረታዊ ጎልማሶች ትምህርት አመቻቾች በማስተማር ስነ-ዘዴ እና በክፍል አያያዝ ዙሪያ ከሰኔ 6-7/2014 ዓ.ም ድረስ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
አቶ ማርቆስ ፍስሃ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመክፈቻው ላይ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት 13 ዓመታት በደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በግብርና፣ በጤና፣ በስነ-ምግብ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በፈጠራ ስራዎች እና በሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም ዩኒቨርሲቲው በትምህርትም ላይ የትምህርትን ጥራት ለማምጣትና መምህራንን ለማብቃት እንዲሁም የተማሪዎችን ውጤት ለማሳደግ የዳሰሳ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ መምህራን እና ርዕሳነ መምህራን በርካታ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ እና ለአቅመ ደካማ ተማሪዎችም የመማሪያ ቁሳቁሶችን እየደጎመ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ጋር በመተባበር መማሪያ ክፍሎችን እያስገነባ መሆኑን አውስተው በዚሁ መሰረትም የዛሬው ስልጠና አንዱ አካል ሲሆን ለሁለት ቀናት በሚቆየው ስልጠና በሲዳማ ክልል ከሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የመሰረታዊ ጎልማሶች ትምህርት አመቻቾች በማስተማር ስነ-ዘዴ እና በክፍል አያያዝ ዙሪያ ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በስልጠናውም ላይ በተጠቀሱት ርዕሶች ላይ100 ሰልጣኞች የተካፈሉ ሲሆን ከንድፈ ሀሳብ ስልጠና በተጨማሪ ሰልጣኞች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የእርስ በርስ ልምድ ልውውጥና ክህሎቶችን የማካፈል ተግባር ተኮር ስልጠና በማድረግ በዘርፉ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት እንደሚያሳድጉ የሚጠበቅ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል::