በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወጣቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት እና የባህል ዕሴቶች ሚና ለሰላም በሚል ርዕስ ውይይት ተካሄደ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፕሬዝዳንት ፅ/ቤት እና የዩናይትድ ኔሽን አሶሴሽን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቻፕተር ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የወጣቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት እና የባህል ዕሴቶች ሚና ለሰላም በሚል ርዕስ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ሰኔ3 ቀን 2014 ዓ.ም ውይይት ተካሂዷል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አደቶ በመክፈቻው ላይ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋና የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሲሆን ሀገራችን ውስጥ ካሉ ተቋማት የመማር ማስተማሩን ሂደት በሰላም እያከናወነ ያለ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ገልፀው በዚህ አስከፊ፣ ብዙዎች ስብዕናቸውን ባጡበት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እባካችሁ ብለው በገሰፁ በሚዋረዱበትና የኃይማኖት አባቶች በሚገደሉበት እንዲሁም በተሳሳተና በተንሻፈፈ ትርክት በርካቶች በሚረግፉበት ስለ ሰላም ለመነጋገርና ለመወያየት በመታደላችን ዕድለኞች ነን ብለዋል፡፡ አክለውም የነበሩንን በርካታ ዕሴቶች እየተውን፣ እርስ በርስ መተቃቀፍና መከባበር ቀርቶ እየተገፋፋን ፍቅርን ሰቅለን ጥላቻን ያነገስንበት ነውና ወዴት እየሄድን ነው የኃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣት ተማሪዎቻችን ሚና ሰላምን ከመገንባትና አማራጭ የግጭት አፈታት ዘዴዎቻችንስ ምን ይመስላሉ በሚሉት ላይ በመወያየትና ተማሪዎቻችንም በሚቀጥሉት ወራት በዚህ ላይ ጥናቶችን እንያደርጉ የምናስጀምርበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
ተማሪ አናንያ ሞገስ የዩናይትድ ኔሽን አሶሴሽን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቻፕተር ም/ፕሬዝዳንት ሰላምና የወጣቶችሚና፣ አማራጭ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም ሰላምን ሰላምን ማስፈን እንዲሁም ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና አካባቢያቸው የሚፈጠሩትን ችግሮች በመፍታትና ሰላምን በማምጣት ያላቸው ሚና በሚሉ ሃሳቦች ላይ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ በቀጣይም ምርምሮችን ለመስራት የታሰበ የውይይት መድረክ መሆኑን ተናግራለች፡፡
በፕሮግራሙም የዩናይትድ ኔሽን አሶሴሽን በኢትዮጵያ ዳይሬክተር፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአቤነዘር ህፃናት ማሳደጊያ መስራች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን በመድረኩም ስለ ሰላምና በአማራጭ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ ውይይትና ምክክር ተካሂዶ በቀጣይ ወራትም ተማሪዎች በተነሱት ርዕሶች ላይ ምርምሮችን ይሰራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልፆአል፡፡