አዲስ ለገቡ ሴት ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ አቀባበል ተደረገላቸው ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ህፃናት ወጣቶችና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመድበው ለሚመጡ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም በማዘጋጀት በግንቦት 16/2014ዓ.ም አቀባበል አደረገ፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ለተማሪዎቹ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ትውልድ እና የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብለው ከተለዩት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደመሆኑ ከዚህ በፊት እንደተለመደው እናንተን ጨምሮ ከ32 ሺህ በላይ ተማሪዎች በመደበኛው እና በተከታታይ ትምህርት ስላሉን አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገን የማማር ማስተማር፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎቻችንን እየሰራን ሲሆን እናንተም በዚህ ዩኒቨርሲቲ መማራችሁ ትልቅ ዕድል በመሆኑ ያላችሁን ጊዜ፣ እውቀትና ክህሎት ለመጣችሁለት ዓላማ እንድታውሉ እንዲሁም ይህ ዕድሜያችሁ በተለያዩ አላስፈላጊ ነገሮች እንድትጠመዱ እና እንድትሳቡ የሚገፋፋ በመሆኑ እራሳችሁን ተቆጣጥራችሁ ለራሳችሁ፣ ለቤተሰባችሁ እና ለሀገራችሁ መሰረት የምትጥሉበት በመሆኑ እራሳችሁን እንድትጠብቁ አደራ እያልኩኝ የትምህርት ጊዜያችሁ የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊው ትብብር እንደሚደረግላችሁ ላሳውቃችሁ ወዳለሁኝ ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ምህረት ገነነ የሴቶች ህፃናት ወጣቶችና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በበኩላቸው እንደተናገሩት የዚህ ፕሮግራም ዋና ዓላማ ተማሪዎች በቆይታቸው እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ፣ አጋላጭ ከሆኑ አደገኛ ባህሪያት ራሳቸውን መጠበቅ እንዲችሉ፣ ለስነ-ተዋልዶ ጤና ችግር እንዳይጋለጡ ራሳቸውን መጠበቅ እንዲችሉ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዳይደርሱባቸው እንዲሁም ቢደርሱባቸውም ምን ማድረግ እንደሚችሉ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የታሰበ መሆኑን ተናግረው ተማሪዎችም ቆይታችሁ የሰላምና የስኬት እንዲሆን እመኛለሁኝ ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙም ስለ ሕይወት ክህሎት እና ተሞክሮዎቻቸው ሴት ውጤታማ መምህራኖች ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ያቀረቡ ሲሆን በቀጣዩ ቀንም አዲስ የገቡ ወንዶች እና ሴቶች ተማሪዎች በጋራ የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም እንደሚዘጋጅላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡