የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከም/ቴ/ሽ/ም/ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ጋር በመተባበር ዓመታዊ የምርምር አውደ ጥናት በግንቦት 5/2014ዓ.ም አካሄደ፡፡
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አንተነህ ጋዲሳ እንደተናገሩት ዛሬ በሚካሄደው ዓመታዊ የምርምር አውደ ጥናት በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተደርጎባቸው በዩኒቨርሲቲው ገንዘብ ድጋፍና በትብብር ፕሮጀክቶች የተሰሩ ምርምሮች የሚቀርቡበት ሲሆን በቀረቡት የጥናት ውጤቶች ላይ ውይይትና አስተያየት ከመስጠት በዘለለ በኮሌጃችን ምርምሮች የሚሰሩት በጤናው እና በሕክምናው ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲያመጡ በመሆኑ የጥናት ውጤቶቹ ሲቀርቡ ከአካዳሚክ ስታፍ በተጨማሪ በዘርፉ እያስተዳደሩ ያሉ የክልሎችና የወረዳዎች ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካለት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳሬክቶሬት የተጋበዙ በመሆኑ የጥናት ግኝቶቹ ተደራሽ እንዲሆኑ ወደ ማህበረሰብ አገልግሎት ለማስገባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመወያየት የታሰበ አውደጥናት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር አስተባባሪ ዶ/ር ሁናቸው በየነ እንደገለፁት በአውደ ጥናቱ ተመራማሪዎች በካንሰር፣ በእናቶችና ህፃናት፣ በሆስፒታሉ አግልግሎት አሰጣጥ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ተያያዥ የጤና ነክ የሆኑ የምርምር ውጤቶች የሚቀርቡ ሲሆን ከባለድርሻ አካላት እና ተሳታፊዎች ጋር በተነሱ ርዕሶች ከመወያየት በዘለለ ምን እየተሰራ እንደሆነ እንዲያውቁት እና ወደፊትም ለሚተገበረውና ለተፈፃሚነቱ ተባባሪ እንዲሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክም ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ሁናቸው አክለውም የተሰሩ የምርምር ስራዎችም በአብዛኛው በሳይንቲፊክ ጆርናሎች የወጡ ሲሆን ቀሪዎቹም እንዲታተሙ እንደሚደረጉና ወደማህበረሰብ አገልግሎትም ተቀይረው ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ቀጣይ ስራዎች የሚሰሩ ሲሆን ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በአውደጥናቱ ከተመራማሪዎቹ በተጨማሪ ከሲዳማና ደቡብ ክልሎች የጤና ቢሮ፣ ከህበረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከተለያዩ ሆስፒታሎች፣ ጥናቱ ከተሰራበት አካባቢ የወረዳ ጤና ፅ/ቤት እና ገጠር ሆስፒታሎች የተጋበዙ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተገኙበት ሲሆን 22 የምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው ፕሮግራሙ መጠናቀቁን ካገኘነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡