በአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ሀገር አቀፍ የምርምር አውደ ጥናት አካሄደ።
አውደ ጥናቱ "Improving business environment and institutions for better investment, tourism and sustainable development in Ethiopia." በሚል ርዕስ የተካሄደ ሲሆን ከተለያየ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተመራማሪዎች ተሳትፈው 17 የሚሆኑ የምርምር ወረቀቶች ቀርበዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጽ/ቤት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ የአለም ባንክ ሀገሮች ቢዝነስን ለመጀመር ያላቸውን ምቹነት ለማወቅ በቅርቡ ባካሄደው ጥናት ኢትዮጵያ ከ193 ሀገራት በ159ኛ ደረጃ ላይ መገኘቷን ገልጸዋል። ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ ለመጀመር ብዙ የቢሮክራሲ፣ የፖሊሲ፣ የብድር ስርዓት እና የመሰረተ ልማት አቅርቦት ፈተናዎች መኖራቸውን የሚያሳይ በመሆኑ በየዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን አስተካክሎ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጉዞ ለማሳለጥ ከአውደ ጥናቱ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ወገኔ ማርቆስ በበኩላቸው በዚህ አውደ ጥናት በዋናነት የሀገሪቱ የንግድ ስርዓት አካሄዱ ምን እንደሚመስል፣ ምን አስቻይ ሁኔታዎች እና ምን ማነቆዎች እንዳሉ በተለያዩ ምርምሮች የተገኙ ውጤቶች እንደሚቀርቡና በምርምሮቹ የተገኙ ውጤቶችን እንደ የፖሊሲ ግብዓት በመጠቀም የንግድ ተቋማትን ለማጠናከር፣ አሳሪ ህጎችን ለማሻሻል እና ዘመናዊ የንግድ ስርዓትን ለማሳደግ በርካታ ልምድ ይወሰድበታል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
በዕለቱ ምርምሮቻቸውን ካቀረቡት ተመራማሪዎች አንዱና በወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ተገኝ ንጉሴ በዕለቱ ስላቀረቡት የምርምር ስራ በገለጹበት ወቅት እንደ ሀገር የኦንላይን ቢዝነስ ወይም ኢንተርኔትን በመጠቀም የሚደረግ ግብይት በሰፊው የማይተገበርና ብዙ ውስንነቶች ያሉበት መሆኑን አስረድተው ለዚህ እንደ ምክንያትነት የቴሌኮም ዘርፉን አለመዘመን፣ የመብራት መቆራረጥ እና ለቴክኖሎጂ ያለን አሉታዊ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ከዋነኞቹ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ተመራማሪው በመጨረሻም የኦንላይን ቢዝነስ መረጃን ለአምራቾች እና ተጠቃሚዎች በእኩል ሰዓት እና በፍጥነት የሚያቀርብ እንዲሁም ያለ ወሰን ተደራሽ የሚያደርግ በመሆኑ በመንግስትና በቢዝነስ ተቋማት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።