የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ።

ግንቦት 01 ቀን 2014 ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ በበጀት አመቱ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ላይ ግምገማና ውይይት በተካሄደበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨሲቲዎች የተቋቋሙበትን አላማና ግብ ለማሳካት እንዲችሉ ከሚያደርጉ ተግባራት አንዱና ዋነኛው የረዥምና የአጭር ጊዜ እቅድ ማዘጋጀትና የታቀዱትን እቅዶች በየጊዜው በመገምገም ያሉበትን ደረጃ መለየትና ማሻሻያዎችን በማድረግ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም እንደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል የሩብ አመትና የግማሽ አመት አፈጻጸም ግምገማ ያካሄደ መሆኑን አስታውሰው የዛሬው የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአመቱ ለመስራት ከታቀዱት ተግባራት ምን ያህሉን ለማከናወን ቻልን፣ ያልተከናወኑ ምን ምን ተግባራት ይቀሩናል፣ በቀጣይስ ምን ማከናወን ይጠበቅብናል የሚሉትን እንዲሁም ባጋጠሙ ችግሮችና ተግዳሮቶች ዙሪያ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ፍሰሀ ጌታቸው በበኩላቸው በ2014 በጀት አመት የመማር ማስተማሩን ስራ ለማሳለጥና በትምህርት ጥራት ላይ የሚታዩ አሉታዊ ክፍተቶችን ለመሙላት ዩኒቨርሲቲው በአመታዊ እቅዱ ውስጥ በማካተት በትኩረት ከሰራባቸው ዘርፎች መካከል መሆኑን ገልጸዋል። ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ በምርምር ዘርፍ በቁጥር እና በይዘት የምርምሮችን ደረጃ ለማሳደግ፣ በማህበረሰብ አገልግሎቱ ብዙዎችን ለመድረስና ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ በርካታ መንገዶችን በመቀየስ በአመታዊ እቅዱ ሲተገበሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል። ዶ/ር ኢንጂነር ፍሰሀ በማጠቃለያቸውም በዛሬው ግምገማ የሚነሱ ሀሳቦችን በማካተት የበጀት አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት በፍጥነት ሊሻሻሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ በማድረግ አመቱን በተሳካ አፈፃፀም ለመጨረስ መታሰቡን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕላንና ተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ቡርቃ በዕለቱ የዩኒቨርሲቲውን የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ገለጻ ባደረጉበት ወቅት በአመቱ በመማር ማስተማር ከሚጠቀሱ በጎ አፈጻጸሞች መካከል ሀገራችን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ላይ በነበረችበት ወቅት የተቀበልናቸውን የአንደኛ አመት ተማሪዎች አንደኛ ሴሚስተርን ጨርሰው፤ ሁለተኛ ሴሚስተርን ወደ ማገባደድ እንዲደርሱ ማስቻል ይጠቀሳል ብለዋል። ከመማር ማስተማር በተጨማሪ የምርምር ስራዎቻችን በዋነኝነት የማህበረሰብ ችግር ፈቺ፤ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከሀገር አቀፍ እና አለም አቀፍ አጋሮች ጋር በጋራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።  ዳይሬክተሩ ከዛሬው ግምገማ ምን እንደሚጠበቅ ሲገልጹ በበጀት አመቱ የታዩ ጠንካራ አፈጻጸሞችን ማሳደግ እንዲሁም ደካማ አፈጻጸም የታየባቸውን ዘርፎች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥና ተፈጻሚ ማድረግ ዋነኞቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመጨረሻም በዕለቱ ከተሳታፊዎች በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠ በኃላ የዕለቱ መርሀ ግብር ተጠናቋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et