የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የኪነ-ሕንፃና የከተሞች ልማት ጥናቶች ተቋማዊ የምክክር ወርክሾፕ ተካሄደ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን ሀገር አቀፍ የኪነ-ሕንፃና የከተሞች ልማት ጥናቶች ተቋማዊ የምክክር ወርክሾፕ ለሁለት ቀናት ማለትም ከሚያዚያ28-29/2014 ዓ.ም ድረስ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካሄደ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የም/ቴ/ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ ሁላችንም እንደምናውቀው በዘርፉ ውስን ምሩቃን እና የግንባታ ቁሳቁሶች እጥረት በመኖራቸው እንዲሁም በሙያው የተደራጁ ባለሙያዎች ማህበር ባለመኖሩ፣ በከፍተኛ የት/ት ተቋማት በቂውን ያህል ምሁራን ባለመኖራቸው የባለሙያ የርስ በርስ ልምድ ልውውጥ ማድረግ ባለመቻሉ በዘርፉ ኪነ-ሕንፃና የከተሞች ልማት ጥራት ላይ ተግዳሮቶች እየገጠሙን ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ዶ/ር ታፈሰ አክለውም የዚህ መሰሉ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በዘርፉ ተበታትነው የሚገኙትን አቅሞች ለማስተባበር እና ተቋማዊ መልክ በማስያዝ አቀናጅቶ ለመጠቀም በዘርፉ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶችን ለመምከርና በጥናት በጋራ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማምጣት አስፈላጊና ጊዜውን የጠበቀ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪና መምህር ዶ/ር ኢንጅነር እሸትአየሁ ክንፈ ከተሳተፉ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ጋር በጋራ ዘላቂ የሆነ ኪነ-ሕንፃና የከተሞች ልማት ጥናቶችና ምርምሮችን ፣ የቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ጉዳዩ ለእኛም አዲስ እንደመሆኑ በቅድሚያ ዘርፉ ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች እንዲመራ፣ በምን መልኩ እንደምንተባበር፣ በት/ትና ስልጠና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆንና እንዲስፋፋ ምን አይነት የትምህርትና ተቋማዊ ስርዓት እንዘርጋ የሚለውን በጋራ በመምከር በቀጣይ የጋራ የሆነ ስትራቴጂክ ሰነድ ለማዘጋጀት፣ የምርምር ውጤቶችን ለማሳተምና ተደራሽ ለማድረግ እና ተፈፃሚም ለማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል፡፡
በፕሮግራሙም ላይ ከሀዋሳ፣ ከአርባምንጭ፣ ከአዲስአበባና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኢትዮጵያ ኪነ-ሕንፃ፣ ሕንፃ ግንባታና ከተማ ልማት፣ ከሲዳማና ደቡብ ክልል ከተማ ልማት ቢሮዎች ተመራማሪዎች፣ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን በተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች ላይም ያሉትን መልካም አጋጣሚዎችን እና ተግዳሮቶችን በመወያየትና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡