በኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የሚመክር ጉባኤ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ከፍሬድሪክ ኤበርት ስቲፈንግ (Friedrich-Ebert- Stiftung) ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ የወደፊት ሁኔታን በሚወስኑ በሀገር አቀፍና በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የኢኮኖሚ እውነታዎች ላይ ያተኮረ በኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የሚመክር ጉባኤ በሚያዚያ 28/2014ዓ.ም በሀዋሳ ሀይሌ ሪዞርት አካሄደ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የም/ቴ/ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በመክፈቻው ላይ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ኢንዱስትሪዎች በሳይንሳዊ እውቀትና ቴክኖሎጂ ካልታገዙ ውጤታማ ሊሆኑ ስለማይችሉ ከዚህ አንፃር ሀገራችን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለመሆን ያቀደችውን የልማት ዕቅድ ለማገዝ በተለዩት ቁልፍ የመንግስት ልማት ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አይሲቲ፣ በቱሪዝምና በማዕድን እንዲሁም በሌሎች አስቻይ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡ በማከልም ሀገራችን ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ተርታ ለማሰለፍ መዋቅራዊ ለውጥ በማድረግ ግብርናው በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ድርሻ መቀነስ የሚያስፈልግ ሲሆን ይሄንን ደግሞ ለማሳካት ጠንካራ፣ ተፎካካሪና ጥራት ያላቸውን ምርቶች የሚያመርቱ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይሄንንም እውን ለማድረግ በዘርፉ በርካታ ያልተፈቱ ችግሮች ያሉ በመሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው የየራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደብረወርቅ ደበበ በበኩላቸው እንደተናገሩት በጉባኤው አምራቾች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ተመራማሪዎች አንድ ላይ በመሆን የሚመክሩበት እንዲሁም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተመራማሪዎችም በጥናታዊ ፅሁፋቸው በዘርፉ ያሉ ፖሊሲዎች ምን እንደሚመስሉ፣ በዘርፉ ያጋጠሙ የሀገር ውስጥና የውጪ ተግዳሮቶችና ችግሮች እንዲሁም የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያቀርቡ ሲሆን ከዚህ የሚገኘውን ግብዓትም በመሰብሰብና በመሰነድ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆን የምናስረክብ ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡
በጉባኤውም ከዲላ፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ ከሲዳማና ደቡብ ክልል ኢቨስትመንት፣ ጥቃቅንና አነስተኛ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርክና ከሞሐ ለስላሳ መጠጦች ድርጅት ተሳታፊዎች የተካፈሉ ሲሆን በቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ ላይም ውይይትና ገንቢ ሀሳቦች ተነስተው ጉባኤው መጠናቀቁን ካገኘነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡