የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ በዓል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በድምቀት ተከበረ።
ሚያዚያ 19/2014 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የተከበረው ይህ ፕሮግራም በሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት የተከፈተ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው የሲዳማ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ስዩም ዩንኩራ በዕለቱ ስለነበረው ፕሮግራም ይዘት በገለጹበት ወቅት በርካታ የጥበብ ስራዎችን ጨምሮ ስለ ጥናት ተቋሙ ተግባራት ምንነት፣ የፍቼ በዓል ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ስለሚኖረው ሚናና የሲዳማ የሉዋ የዘመን አቆጣጠር ላይ የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል። አክለውም የጥናት ተቋሙ ከተመሰረተ ገና አንድ አመት ከስድስት ወር ብቻ ቢሆንም ከሲዳምኛ ወደ አማርኛና ኢንግልዘኛ የተተረጎመ መዝገበ ቃላት አዘጋጅቶ ማቅረቡን እንዲሁም በፍቼና ሌሎች የብሔሩ ትውፊቶች ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አዳቶ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የፍቼ ጫምባላላ በዓል የሲዳማ ብሔር መገለጫ ብቻ ከመሆን አልፎ በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ላይ በመመዝገብ አለምአቀፋዊነትን ተላብሷል ብለዋል። ይህ ባህል በርካታ ድንቅ እሴቶችን በውስጡ የያዘ መሆኑን ገልጸው ውብ የሆነው የቄጣላ ስርዓት ብዙ መገለጫዎች ያሉትና የእኩልነት ማሳያ የሆነው የሻፌታ ስርዓት የብሔሩ ሽማግሌዎች ስለሀገራቸው ፈጣሪን የሚለምኑበት ክዋኔን ለማሳያነት አቅርበዋል። እንደ ዩኒቨርሲቲ ባህላዊ እሴቶችን በምርምር በማበልጸግ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዕለቱ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በዩኒቨርስቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ኪንኪኖ ኪአ በበኩላቸው የፍቼ ጫምባላላ በዓል የአንድነት፣ የመከባባር፣ የፍቅር እና የይቅርታ በዓል እንደመሆኑ እንደ ሀገር የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል። በዚህ ባህል ውስጥ የሚገኙትን እንደ ‘አፍኒ’ ያሉ የይቅርታ ስርዓቶችን እንዲሁም መከባበርንና ሰላምን የሚሰብኩ በርካታ እሴቶችን በመጠቀም እንደ ሀገር የገጠመንን ፈተና ለመሻገር መጠቀም እንደሚገባና ለዚህም ደግሞ ምሁራን በእነዚህ ትውፊቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ እና ልማት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ የሲዳማ ብሔር ስለሚጠቀሙበት የሉና የቀን አቆጣጠር ላይ የተደረገ ጥናትን ባቀረቡበት ወቅት የሲዳማ ብሔር ጠበብቶች የጨረቃንና የከዋክብትን አቀማመጥ በማጥናት የራሳቸው የሆነ የዘመን አቆጣጠርን መቀመር መቻላቸውን ገልጸዋል። የሲዳማ ህዝብ ከአንድ አመት ወደ ሌላ አመት የሚሸጋገርበት ሁሉቃ የተሰኘው ስርዓት በውስጡ ብዙ ሳይንሳዊ ትርጓሜ የያዘ እና ላለፉት 1800 አመታት ሲተገበር የቆየ የዘመን አቆጣጠር በመሆኑ ይህንንና መሰል ሀገር በቀል እውቀቶችን በምርምር መደገፍ እና ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ይህን መሰል ዝግጅቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ስለ ፍቼ ጫምባላላ በዓል የሚታዩ ብዥታዎችን ለማጥራትና ይህን አስደማሚ ባህል በጋራ ለማክበር እንዲሁም በሀገር አቀፍ ብሎም በአለምአቀፍ ደረጃ ሊኖረው የሚገባውን አዎንታዊ ድርሻ ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል። በመጨረሻም ፕሬዝዳንቱ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ በዕለቱ የተዘጋጀውን ሻፌታ የሀገር ሽማግሌዎች በመቁረስ ለተሳታፊዎች እንዲቀርብ አድርገዋል።