የማህበራዊ ሳይንስና ሰነ-ሰብ ኮሌጅ አራተኛውን ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ አዘጋጀ።
ከሚያዚያ 7-8/2014ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት “Enquiry into socio-cultural changes and Development in Ethiopia" በሚል ቃል በተካሄደው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ሰነ-ሰብ ኮሌጅ ኮንፈረንስ ላይ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዳኜ ሽብሩ ከ100 በላይ ተሳታፊዎች ከሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ እንዲሁም የተመረጡ 25 የሚጠጉ የምርምር ስራዎች እንደሚቀርቡ ተናግረው፤ የሚገኙ ውጤቶችም ለፖሊሲ ግብአትነት፣ አንገብጋቢ የማህበረሰቡ ችግሮችን ለመፍታት እና በተለያዩ ጆርናሎች ላይ ቀርበው ለብዙዎች ተደራሽ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ምደባ እና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት የተከበሩ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ የሀገራችን ህዝቦች በጣም የተሳሰረ እና የሚያመሳስላቸው ማህበራዊ መስተጋብር መኖሩን ገልጸዉ ይህም በተለያዩ ወቅቶች በሀገር ውስጥ እና በውጭ አካላት ለሚመጡ ተጽዕኖዎች ሳይበገሩ በጽናት እንዲቆሙ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደ ማህበረሰብ እያጋጠሙ ለሚገኙ የእሴት መሸርሸሮች ምክንያታቸውን ለመለየትና ዘላቂ መፍትሄ ለማስቀመጥ መሰል ውይይቶች አይነተኛ ሚና እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር መለሰ ማዳ ዩኒቨርሲቲዎችና ምሁራን ያመጡትን የምርምር ውጤት ተቀብሎ ወደ ተግባር ለመለወጥ በመንግስት ደረጃ የሚገኙ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው እና ተባባሪ ሊሆኑ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበው በቀጣይ ውይይት የተደረገባቸው የምርምር ስራዎች ለህትመት እንደሚበቁና ለብዙዎች ተደራሽ እንደሚደረጉ ገልጸው ምርምሮቹ በአብዛኛው በድህነት ቅነሳ፣ እድገት፣ ባህልና ቱሪዝም እና መሰል ዘርፎች ላይ ያተኮሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሰቲ የጆርናሊዝም እና ኮሚኒኬሽን ት/ክፍል መምህር የሆኑትና በዕለቱ ታዳሚ የነበሩት አቶ መኮንን ኃ/ማርያም ሲናገሩ አሁን በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠን እና በይዘት እየሰፉ እንደሚገኙ እና ለእነዚህ አንገብጋቢ ችግሮች በጊዜ መፍትሄ የማይበጅላቸው ከሆነ ስር በመስደድ የማህበረሰብ ቀውስ ወደ ማስከተል ሊያድጉ እንደሚችሉ ጠቁመው እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ማለትም ህብረተሰቡ፣ የፖለቲካ ኤሊቶች፣ ምሁራንና የማህበረሰብ አንቂዎች ችግሮችን ከራስ ለማሸሽ የሚደረግ ያልተገባ አካሄድን ወደ ጎን በመተው ድርሻቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆንና መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።