ለሶስተኛ ድግሪ ተማሪዎች የአቅም ግንባታ እና ክህሎት ስልጠና ተሰጠ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ በስታስቲክስ ትምህርት ክፍል አስተባባሪነት በዩኒቨርሲቲው ለሚገኙ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ለሚማሩ ሶስተኛ ድግሪ ተማሪዎች ለሚሰሩት የምርምር ጥናቶች የሚጠቅሙ ሶፍት ዌሮችን በመጀመሪያው ዙር ለ45 ተማሪዎች ከመጋቢት 29-30/2014 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
ዶ/ር ሰላማዊት ሲርካ ሰልጠናውን ከሚሰጡት አስላጣኞች አንዷ ሲሆኑ ስልጠናው ለሶስተኛ ድግሪ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች እንደየፍላጎታቸው ለሚሰሩት ምርምሮች የሚጠቅማቸውን የሶፍት ዌር ክፍሎታቸውን ለማሳደግ የሚረዳ ሰልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልፀው ጥሩ ምርምር ለመስራት ደግሞ በዚህ መሰሉ ስልጠና የዳታ አይነት፣ የዳታ ተፈጥሮ እና አተናተን ክህሎት የሚዳሰስ በመሆኑ ጠቃሚ ስልጠና መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው በመስጠት የተሳተፉት ሌላኛው አሰልጣኝ በኮሌጁ የም/ቴ/ሽግግር ተባባሪ ዲን የሆኑት ዶ/ር ደረጀ ደንቤ ደግሞ ተማሪዎቹ የምርምር ወረቀቶችን ስለሚሰሩና የዚህ መሰሉ ስልጠና አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘን ያለባቸውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት እና ነፃ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ተናግረው የሶስተኛ ድግሪ ተምሪዎች በተለያዩ ዙሮች ሰልጥነው ከጨረሱ በኃላ ለሁለተኛ ድግሪ ተማሪዎችም ስልጠናው እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮና ኮምፒቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዘይቱ ጋሻው በተለያየ ግዜ በርካታ ተማሪዎች ትምህርት ክፍሉን ስልጠና እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሰረት ከዚህ በፊት በተናጠል ይሰጥ የነበረው የ R, SPSS እና STATA ሶፍትዌር ሰልጠና በተጠናከረ ሁኔታ በነፃ እየተሰጠ እንደሆነ ገልፀው ወደፊት ጥያቄው በርካታ እንደመሆኑ ከአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ ፕሬዚዳንት እና ከም/ቴ/ሽግግር ም/ ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት ጋር በመነጋገር እና በመተባበር ስልጠናው በሰፊው መሰጠት እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ሰልጣኝ ተማሪዎቹም እየተሰጣቸው ባለው ስልጠና ደስተኞች መሆናቸውን ገልፀው የዚህ መሰሉ የክህሎት ስልጠና ወደሚፈልጉት ግብ ለመድረስ አስተዋፆው የጎላ በመሆኑ ስልጠናውን ላመቻቸላቸው ትምህርት ክፍል እና አሰልጣኞች ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡