የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በተለያዩ የቋንቋ፣ የአመራርነትና የሳይንስ ትምህርቶች ላይ ለመምህራንና ትምህርት አስተዳደር አካላት ስልጠና ሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር ከትምህርት መምሪያው የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችና ከሐዮሌ የትምህርት ማዕከል ለተወጣጡ መምህራን አመራር አካላት በቋንቋ፣ በትምህርት ሥራ አመራርነት፣ በሒሳብ፣ በኬሚስትሪ፣ በባዮሎጂ እና በፊዚክስ የትምህርት አይነቶች ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና መጋቢት 10 እና 11 ቀን 2014 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ሰጥቷል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጽ/ቤት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ ስልጠናውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከምስረታው ጀምሮ አሁን እስከደረሰበት ባሉት ጊዜያት በርካታ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ችግር ፈቺ ምርምሮችና በበርካታ የማህበረሰብ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ ሚናውን ሲወጣ መቆየቱን ገልጸዋል። አክለውም በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ መምህራን 60% የሚሆነውን ጊዜያቸውን በማስተማር፣ 25% የሚሆን ጊዜያቸውን በምርምር ስራ ላይ እና 15% የሚሆነውን የተቀረውን ጊዜያቸውን ደግሞ በማህበረሰብ አገልግሎት ላይ እንደሚያውሉ ገልጸው የመምህራንን የማስተማር ስነ-ዘዴ እና የቤተ-ሙከራ አጠቃቀም ክህሎትን ለማሳደግ ያለመ ስልጠና መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጽ/ቤት የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ፍሰሀ በበኩላቸው የዛሬው ስልጠና የተዘጋጀው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ በጠየቀው ጥያቄ መሰረት የተሰጠ ስልጠና መሆኑን ተናግረው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬቱ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በለያቸው ሰባት በሚደርሱ የቴክኖሎጂ መንደሮች ላይ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የህብረተሰቡን ችግር ባማከለ መልኩ መፍትሄዎችን በመቅረጽ አዎንታዊ ሚና ሲጫወት መቆየቱን አብራርተዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና በዕለቱ ስልጠናውን ከሰጡ አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ከድር ወልይ እንደተናገሩት ስልጠናው መምህራን እንዴት ተማሪዎቻቸውን ቀለል ባለና ውጤታማ በሆነ ዘዴ ትምህርትን መቀበል እንዲችሉ የሚያደርጋቸውን መንገድ የሚፈጥር መሆኑ ታውቋል። አክለውም በተለምዶው በአመዛኙ በንድፈ ሀሳብ ወይም Theory ላይ የተመሰረተውን የሀገራችንን የማስተማር ስነ-ዘዴ በተግባር ትምህርት ላይም የተደገፈ ይሆን ዘንድ መምህራን እንዴት ቤተ-ሙከራዎች መጠቀም እንደሚገባቸው ልምድ የሚሰጥ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ሌላው ስልጠናውን የሰጡ በሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አለማየሁ ጳውሎስ ሲናገሩ ስልጠናውን የተካፈሉ መምህራን በንድፈ ሀሳብ የተማሯቸውን በርካታ ትምህርቶች እንዴት በቤተ-ሙከራ ውስጥ በተግባር መስራት እንደሚችሉና ይህንንም ክህሎት በመያዝ በሚያስተምሩባቸው ት/ቤቶች ለሚገኙ ተማሪዎች ሊያሳዩ እንደሚችሉ ልምድ የሚቀስሙበት ነው ብለዋል። መምህራን በቀጥታ ከተማሪዎች ጋር የሚገናኙ እንደመሆናቸው መጠን የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ ላይ አይነተኛ ሚናን ስለሚጫወቱ መሰል ተከታታይነት ያላቸው እና ሌሎች መምህራንንም የሚያሳትፉ ስልጠናዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል።