የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ አዘጋጀ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ በ2012 ዓ.ም እና በ2013 ዓ.ም በኮሌጁ መምህራን በተሰሩ እንዲሁም እየተሰሩ ባሉ ምርምሮች ላይ ለመወያየትና በምክክር እንዲዳብሩ ለማድረግ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ አዘጋጅቷል፡፡
የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደብረወርቅ ደበበ እንደተናገሩት በዛሬው ዕለት 9 ዲሲፕልነሪ፣ ቴማቲክ እና የትብብር ምርምሮች የሚቀርቡ ሲሆን የጥናት ውጤቶቹ ላይም ተወያይቶ በማዳበር በቀጣይ በኮሌጁ ሁለት ጆርናሎች ላይ ታትመው እንዲወጡ ተደርገው ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ የታሰበ እና ወጣት ተመራማሪዎቻችንም ከአንጋፋዎቹ ልምድና ዕውቀት በማዳበር ለፖሊሲ ግብዓቶች፣ ችግር ፈቺ እና የመፍትሔ አቅጣጫን የሚያመለክቱ ምርምሮችን እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
ዲኑ አክለውም በቀጣይም የምርምር ተቋም እንደመሆናችን አቅማችንን በማጎልበትና ልምዳችንን በማዳበር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ፣ በሰላም ዙሪያ፣ በሕግና ፍትህ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በዲሞክራሲ ግንባታ፣ መልካም አስተዳደርና ፌደራሊዝም በመሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው በመሳተፍና ጥናቶችን በማድረግ የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይኖርባናል ብለዋል፡፡
የኮሌጁ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተባባሪ ዲን ተወካይ መምህር ከድር ዳሮ በበኩላቸው ጉባኤው የመምህራንን የምርምር ተሳትፎ ለማጉላት፣ የሚስተካከሉ ካሉ ተስተካክለው እንዲቀርቡ ለማድረግ እና የጥናት ውጤቶቹንም በዩኒቨርሲቲው ፕሮሲዲንግ ላይ ታትመው እንዲወጡ ለመገምገም የሚረዳን ሲሆን ሁሉም የኮሌጁ መምህራኖችም በምርምር ስራዎች በንቃት ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንዲሁም የምርምር ግምገማ ጉባኤው ላይ በመታደም እንዲወያዩ አሳስበዋል፡፡
በፕሮግራሙም ላይ ምርምሮቹ ቀርበው ውይይትና ገንቢ ኃሳቦች ተሰጥቶባቸው ጉባኤው መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡