ለሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ለሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ ቤት የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያና ከሐዮሌ የትምህርት ማዕከል ለተወጣጡ 112 የሁለተኛ ደረጃ ት/ ቤት መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ።

የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ ስልጠናውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በግብርና፣ ጤና፣ትምህርትና ሌሎች በርካታ ዘርፎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ስልጠናዎችንና የብቃት ማሻሻያዎችን ለማህበረሰቡ ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል። አክለውም የአሁኑ ስልጠና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየተሰራ ለሚገኘው ስራ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትና ዩኒቨርሲቲው በቀጣዩ ሳምንትም በማስተማር ስነዘዴ፣ የፈጠራ ክህሎትን በማሳደግ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ስልጠና ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ማርቆስ ፍሰሀ በበኩላቸው የዕለቱ ስልጠና ለ257 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራንና የት/ቤት አመራሮች እንዲሰጥ ከታቀደው የመጀመሪያው ዙር መሆኑን አመላክተው ስልጠናው የተዘጋጀው የመምህራንን የማስተማር ብቃት እንዲሁም የትምህርት አመራሮችን የአመራር ክህሎት ለማሳደግ በማሰብ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ የቀረበውን ጥያቄ መሰረት አድርጎ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በማስከተልም የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከለያቸው ስድስት የቴማቲክ ዘርፎች አንዱ በሆነው የትምህርት ዘርፍ ላይ በየጊዜው በጥናት የተለዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ሲሰጥና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ሲያመላክት መቆየቱን ገልጸዋል።

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የትምህርት መምሪያ የመምህራን ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዳነ አብርሃም ሲናገሩ መስሪያ ቤታቸው በተለያዩ ጊዜያት ለዩኒቨርሲቲው የሚያቀርባቸውን የስልጠናና የሙያ ማሻሻያ ድጋፍ ጥያቄዎች ዩኒቨርሲቲው ቀና ምላሽ በመስጠትና በፍጥነት ተግባራዊ በማድረግ ለማህበረሰብ አገልግሎት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስመስክሯል ብለዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም ዛሬ ስልጠናውን የሚካፈሉ መምህራንና የት/ቤት መሪዎች ከስልጠናው በሚያገኙት እውቀት ታግዘው የትምህርት ዘርፉ እንዴት መመራት እንዳለበትና እንደ ክልል እንዲሁም እንደ ሀገር ለመድረስ የምንፈልግበት ቦታ ላይ ለመገኘት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል። በመጨረሻም በትምህርት ላይ የሚደረጉ ተግባራት ጊዜ እና ትዕግስትን የሚጠይቁ ውጤታቸውም በጊዜ ሂደት የሚታይ በመሆኑ ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎች እንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል።

መጋቢት 2 እና 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ባለው በዚሁ ስልጠና ላይ ሰልጣኞች በተለያዩ ቡድኖች ተከፍለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት፣ አይ.ሲ.ቲ፣ ቴክኒካል ድሮዊንግ እና ተቋማዊ አመራር ላይ ያተኮሩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እየተከታተሉ ነው።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et