ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በደማቅ ሥነ-ስርዓት ተከበረ።
በዓለም ለ111ኛ ግዜ በሀገራችን ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ’’ በሚል መሪ ቃል በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አደራሽ መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በድምቀት ተከብሯል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ፍስሃ ጌታቸው በዚሁ ወቅት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የበዓሉ ዋነኛ ዓላማ በህብረተሰቡ ውስጥ ለዘመናት የሰረፀውንና በፆታ ላይ የተመሰረተ የሥራ ክፍፍል፤የትምህርት ዕድልና የመቀጠር ምጣኔን በማስቀረት ሴቶችን በእኩልነት ያሳተፈ የጥቅም ተጋሪነት እንዲጨምር፤ቀጣይነት ያለውና ለትውልድ የሚሸጋገር ዕድገት በመምጣት የተረጋጋችና የበለፀገች ሀገር እንድትኖረን አቅጣጫ ማስቀመጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት የሴት ተማሪዎች የቅበላ ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሴቶች ትምህርት በተሰጠው ልዩ ትኩረት በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጠንክረው ከመስራታቸውም በላይ በዩኒቨርሲቲው ሴቶች በመምህርነት ሙያ በብዛት እንዲያገለግሉ ዕድል እንዲሰጥ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚገቡ ሴት ተማሪዎች ከቅበላ ጀምሮ በዘርፉ በተመደቡ ባለሙያዎች የምክርና ክትትል ድጋፎችን በማሻሻል ብዙ ሴት ተማሪዎች በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ መምጣታቸውንና በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ካሉት ተማሪዎች ሴቶች ከፍተኛውን ነጥብ እያስመዘገቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም ከሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ እንቅስቃሴዎች የፆታ እኩልነትን በማረጋገጥ ለመስራት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሠራ መሆኑን ገልጸው ከግብ ለማድረስም ሁሉም የበኩሉን አስተዋጾኦ በማድረግ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ህፃናት ወጣቶችና ኤች አይ ቪ ኤድስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ምህረት ገነነ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በተለይም ከገጠር አከባቢዎች የሚመጡ አብዛኛዎቹ ሴት ተማሪዎች ችግሮቻቸውን በግልጽ ለመናገር ስለሚፈሩ በትምህርታቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር ገልፀው በዳይሬክቶሬቱ ሥር በተቋቋሙ አደረጃጀቶች ተደራሽነትን ማዕከል ባደረገ አሠራር በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ክበቦችና በጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች የሚሳተፉ ሴት ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በማስረጃነት ጠቅሰዋል ፡፡
በተለይም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ሴት ተማሪዎች በቆይታቸው ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ ተመርቀው በሁሉም የዓለም ማዕዘናት ስለሚሰማሩ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ግብረገብነት ይዘው እንዲወጡና በሁሉም ዘርፍ በራሳቸው የሚተማመኑ፤ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ኮሚውንኬሽን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እመቤት በቀለ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበር ታሪካዊ ዳራውንና አሁን ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንደየአከባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ቢለያዩም በማኀበረሰቡ ለረዥም ዘመናት በተገነቡ ኃላቀር አመለካከቶች በተለይም በሀብት ክፍፍል ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መኖሩን በጽሁፉ ተመላክቷል፡፡ በዚህም የተነሳ የዘንድሮው አለምአቀፍ መሪ ቃል “#breakthebias” “አድሎውን እንስበር” የሚል ሲሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ግን “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” የሚል መሆኑ ተወስቷል፡፡
በዕለቱ በዩኒቨርሲቲው በሴቶች ብቻ የተመሰረተው መራሂት የተማሪዎች ክበብ የተለያዩ ድራማዊ ተውኔቶች፤ ግጥምና ጭውውቶችን በማቅረብ ታዳሚውን አዝናንተዋል፡፡ በተጨማሪም ከሁሉም ኮሌጆች በየተለያዩ ዓመታት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን የሁሉም ኮሌጆች ሃላፊዎችና ምክትል ፕሬዚደንቶች በመድረኩ ላይ በመታደም ተማሪዎቻቸውንና ሰራተኞችን ሸልመዋል፡፡ በማስከተልም ከሁሉም ኮሌጆችና የዩኒቨርሲቲው የስራ ክፍሎች የተውጣጡ ትጉ የአስተዳደር ሰራተኞች፤ ለሴት ተማሪዎች በጎ ድጋፍ ያደረጉ ትጉ ሴትና ወንድ መምህራን የዕለቱ ምርጥ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡
በመጨረሻም የዕለቱ ሴት ትሸላሚ መምህራንና ተማሪዎች በሻማ ማብራትና ዳቦ ቆረሳ ለወደፊትም የሴቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወንዶችም አብረው እንዲታገሉ በማሳሰብ ዝግጅቱ ተቋጭቷል፡፡