አድዋን ምክንያት በማድረግ ልዩ ፕሮግራም ተዘጋጀ

የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የምክንያታዊ ባለራዕዮች ስብስብ ክበብ (RVC) የመላው ጥቁር ህዝቦች የድል በዓል የሆነውን አድዋን ምክንያት በማድረግ ልዩ ፕሮግራም አዘጋጀ።

ክበቡ የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ፕሮግራሙን ያዘጋጀው ከተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር  በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ትሪቡን በተካሄደው በዚሁ ልዩ ፕሮግራም ላይ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ካምፓስ እና የቴክኖሎጂ ኮሌጅ ተማሪዎች በብዛት የታደሙበት ሲሆን ከዩኒቨርሲቲው ሌሎች ካምፓሶች የመጡ ተማሪዎችም ተሳታፊ ሆነውበታል።

የምክንያታዊ ባለራዕዮች ስብስብ ክበብ (RCV) ጸሀፊ የሆነችው ተማሪ እፀገነት መልካሙ ክበቡ ከተመሰረተ አስራ አንድ አመታት ያለፉት ሲሆን በእነዚሁ ጊዜያትም ወጣቶች የማንበብና የመናገር ልምዳቸውን እንዲያዳብሩ እንዲሁም በእውቀት እና በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን መከወኑን ገልጻለች። ጸሀፊዋ አክላም የዛሬው ፕሮግራም ወጣቶች ያለፈውን አኩሪ ታሪክ እየዘከሩ፣ ከዚያም ትምህርት በመውሰድ አሁን ላይ ሀገራችን የገጠማትን የአንድነት አደጋ በመቀልበስ የራሳቸውን አድዋ ይጽፉ ዘንድ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግራለች። ክበቡ በተለይ ላለፉት ሶስት አመታት የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ድል የሆነውን ይህን የአድዋ በዓል በተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ በሆኑ መንገዶች እና የጎዳና ላይ ትርዒቶችን በማዘጋጀት በድምቀት ሲያከብር መቆየቱን ተናግራ በየአመቱ ከሚደረጉ መሰል ፕሮግራሞች በተጨማሪም በየሴሚስተሩ የሚካሄዱ ተምሳሌት የሚሆኑ ሰዎችን በመጋበዝ አስተማሪ የሆነውን የህይወት ተሞክሯቸውን ለተማሪዎች እንዲያጋሩ የሚደረግበት ፕሮግራም መኖሩን አብራርታለች።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ አመት የህግ ተማሪ እና የክበቡ የኮሚቴ አባል የሆነችው ተማሪ ባምላኩ ስዩም በበኩሏ ኪነ-ጥበብ የሰዎችን ሀሳብ የመያዝ አቅሙ ትልቅ እንደመሆኑ መጠን ኪናዊ በሆኑ መንገዶች የሚቀርቡት እንደዚህ አይነት ፕሮግራሞች በተሳታፊዎች ዘንድ የመነሳሳት መንፈስን በመፍጠር ለድል መሰረት የሆነውን ሀገራዊ አንድነት ለማጉላት እና ሰዎች በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ አይነተኛ ድርሻ ይወጣል ብላለች። ክበቡ በየሳምቱ ቅዳሜ የሚካሄድ የተመረጡ የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሳት የሚደረግ ነጻ የውይይት ፕሮግራም ያለው ሲሆን ይህም የተማሪዎችን ምክንያታዊነት በማጎልበት ኋላ ቀር የሆነውን ሀሳብን በሀይል የመጫን መንገድ በማስቀረት በሀሳብ ልዕልና የሚያምኑ ምክንያታዊ ወጣቶችን በማፍራት የነገውን የሀገሪቱን መጻይ እድል ብሩህ እንዲሆን ያደርገዋል ብላ እንደምታምን ገልጻለች።

በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስ እና ሰብአዊነት ኮሌጅ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል የሶስተኛ አመት ተማሪው ወጣት አቡበከር አሊሰይድ እንደገለጸው የጀግኖች አባቶቻችን ገድል የሆነው የአድዋ ድል በዓል የመተባበርን እና የአንድነትን አስፈላጊነት ለማስረዳት ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ይህን መንፈስ እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም በልማት እና ሀገራዊ በሆኑ ሁሉም ዘርፎች ላይ አንድነቱን ሊያጎላ እንደሚገባ ተናግሯል። ወጣት አቡበከር በተጨማሪነት ዩኒቨርሲቲ አለም አቀፍ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጲያን ባህል እና ገናናነት ከሀገራችን አልፎ  ለዓለም ለማስተዋወቅ በየዩኒቨርሲቲዎቻችን ስለ ሀገራችን የጋራ አመለካከት እንዲኖረን ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁሟል።

የእለቱ ፕሮግም የተለያዩ ድራማዎች፣ መነባንቦች፣ ግጥሞች እና መሰል የኪነ-ጥበብ ስራዎችን በማቅረብ በድምቀት ተከናውኖ ተጠናቋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et