የምርምር ፕሮግራሞች ዳይሬክቶሬት በተለያዩ ርዕሶች ላይ ለመምህራንና ተመራማሪዎች ስልጠና ሰጠ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ስር የሚገኘው የምርምር ፕሮግራሞች ዳይሬክቶሬት ለዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ምክረ ሃሳብ አፃፃፍ እና በትብብር ክህሎት ላይ ከየካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት ስልጠና ሰጠ፡፡
የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብለው ከተለዩት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደመሆኑ በሀገራችን ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙት 329 ዩኒቨርሲቲዎች ልቆ ለመገኘት እና የምርምር ዘርፉን በወጥነት ለመምራት ችግር የሚፈቱ፣ ዕውቀት የሚጨምሩ እና በአለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ተቀባይነት አግኝተው የሚታተሙ የምርምር ውጤቶችን ልንሰራ ይገባናል ፡፡ ዩኒቨርሲቲውም የምርምር ስራዎች እንዲጎለብቱ የመምህራንን አቅም አቅም ማጎልበት ወሳኝ በመሆኑ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ታወቋል፡፡
ዶ/ር ታፈሰ አክለውም ዩኒቨርሲቲው አሁን ያለበት ቁመና ላይ ለመድረስ የትብብር ፕሮጀክቶች ሚና ላቅ ያለ መሆኑን ጠቅሰው በተገኙት ድጋፎችም በመታገዝ የምርምር፣ የትምህርት ዕድል፣ ከኢንዱስትሪ ጋር የተገናኙ ስራዎች፣ ከማህበረሰብ አገልግሎት ጋር የሚሰሩና ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆኑ ስራዎች በተለያዩ ዘርፎች እየሰራን እንገኛለን ካሉ በኃላ እናንተም የዛሬ ሰልጣኞች ከዚህ በፊት ባላችሁ ልምድ ላይ በዚህ ስልጠና በመታገዝ የትብብር ፕሮጀክቶችን ሳትሰለቹ ተፃፅፋችሁ በማምጣት ዩኒቨርሲቲያችንን እና ሀገራችሁን እንድትደግፉ አደራ እላለሁም ብለዋል፡፡
የምርምር ፕሮግራሞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መብራቱ ሙላቱ በበኩላቸው በዚህ ስልጠና ላይ የተገኙት አሰልጣኞች በዚህ ዘርፍ ደጋግመው በመሞከር ተፈትነው ያለፉና በርካታ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ምሁራን በመሆናቸው ሰልጣኞች በዚህ ስልጠና ተጠቃሚ እንደምትሆኑ እየገለፅኩኝ ስልጠናው የተሳካ እንዲሆን እመኛለሁኝ ብለዋል፡፡