የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ስለኮሌጁ በተደረገ ጥናት ላይ ውይይትና ምክክር አካሄደ

የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ስለኮሌጁ በተደረገ ጥናት ላይ ውይይትና ምክክር አካሄደ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ስለኮሌጁ የመማር ማስተማር ሂደቶች፣ ግብዓቶች እና የምሩቃንን የስራ ዕድል በተመለከተ የኮሌጁ ምሁራን ከባለድርሻ አካላት ጋር ያጠኑትንጥናት ለመወያየት  በየካቲት 23/2014ዓ.ም የምክክር መድረክ አዘጋጀ፡፡

በምክክር መድረኩ መክፈቻ ላይ የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሞቱማ ቶሌራ ኮሌጁ አንጋፋና በዘርፉም በርካታ ምርቃንን ለሀገሪቱ ሲያፈራ የቆየ ቢሆንም በቅርቡ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ወደኮሌጃችን የመጡ ተማሪዎችን የትምህርት ፕሮግራም ምርጫ ታይቶ ኮሌጁን ቅድሚያ ሰጥተው እንደማይመርጡት እና በ2012ዓ.ም ከተመረቁት ተማሪዎች የስራ ዕድል ያገኙት ከ35%  እንደማይበልጡ በመረጋገጡ ስለኮሌጁ ወቅታዊ የመማር ማስተማር ስራዎች፣ ለመማር ማስተማሩ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችና የመቀጠር ምጣኔ ችግርን አስመልክቶ ተጨማሪ ጥናት ተጠንቶና ተሰንዶ በዛሬው ዕለት በውይይት እንዲዳብር ለኮሌጁ አመራሮችና መምህራኖች ቀርቧል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሞቱማ አክለውም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብለው ከተለዩት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደመሆኑ በቀጣይ እኛም ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ትኩረት በመስጠት  በሁለተኛ እና ሶስተኛ ድግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች ላይ እንድንሰራ ስለሚጠበቅብን እንዲሁም በመጀመሪያ ድግሪ ላይም በፕሮግራም አስፈላጊነት፣ የቀጣሪዎችን ፍላጎትና ገበያውን  ያማከሉ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ እና በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥተን በመስራት በዕውቀትና ክህሎት የዳበሩ ምሩቃንን ማፍራት ካልቻልን ተመራጭነታችን ጥያቄ ውስጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙም ላይ የጥናት ኮሚቴው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከኮሌጁ መምህራን፣ ሰራተኞች፣ ተማሪዎች፣ የቅርብ ምሩቃን፣ ባለሙያዎች እና የምርምር ተቋማት በሰበሰበው መረጃ መሰረት የደረሰበትን የጥናት ውጤት ለተሳታፊዎች ያቀረበ ሲሆን ተሳታፊዎችም በቀረበው ሰነድ ላይ በመወያየትና በቀጣይ ጥናቱ ሊያካትት በሚገባው ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡

                                

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et