በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሁለት ወረዳዎች የነፃ ምርመራ አገልግሎት አካሄደ።
በኮሌጁ የማኀበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክቴር ረ/ፕሮፌሰር ዓለሙ ጣሚሶ በሲዳማ ክልል ቡርሳና ሻፋሞ ወረዳዎች ላይ የተካሄዱ ነፃ የህብረተሰብ ጤና ምርመራ ፕሮግራሞችን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግላጫ በአከባቢው ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከሰው ወደ ሰው በንክኪ በማይተላለፉ ስኳርና ግፊት በመሳሰሉ በሽታዎች ተጠቂ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በሽታዎቹ በሚጀምሩበት ጊዜ ምንም ምልክት የማያሳዩ ከመሆናቸውም በላይ ተገቢው ክትትል ካልተደረገ ኩላሊትና ጉበት የመሳሰሉ ሌሎች የአካል ክፍሎች ላይ ጫና በማሳደር በሽተኛው ታክሞ እንዳይድን ከፍተኛ ተጽህኖ የሚፈጥሩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
በሚቀጥሉት 5 ወራት ከ20ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የነፃ ምርመራ አገልግሎት ለማዳረስ መታቀዱንና በዘላቂነትም በሀዋሳ ከተማና በ5 የገጠር ወረዳዎች ከተለያዩ አጋዥ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባር የነፃ ምርመራ ማዕከላትን ለማቋቋምና ለወረዳ ጤና ጥበቃ የዘርፉ ባለሙዎች ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱን ከገለፃው ለመረዳት ተችሏል፡፡
አንዳንድ ተጠቃሚዎች በዚሁ ወቅት በሰጡት አስተያየት አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ጤና ተቋማት በሚሄዱበት ወቅት ወረፋ በመጠበቅ የሥራ ጊዜያቸው የሚባክንና ከአቅም በላይ ክፍያ የሚጠየቁ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች በተገቢው መንገድ እንደማያስተናግዷቸው ገልፀው ይህ በጎ ተግባር ሊቀጥል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በሻፋሞና ቡርሳ ወረዳዎች በተካሄዱ ፕሮግራሞች ከ2 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለመሆን መቻላቸውን ለጤና ምርመራ ከተወሰደው የስም መዝገብ ለማወቅ ተችሏል፡፡