ኢኮኃድሮሎጂን መሰረት ያደረገ የአፈርና ውሃ አያያዝ በሚል ርዕስ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል ኢኮኃድሮሎጂን መሰረት ያደረገ የአፈርና ውሃ አያያዝ በሚል ርዕስ ለባለድርሻ አካላት ከታህሳስ25-27/2014ዓ.ም ድረስ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ጌታቸው ስሜ ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት የስምጥ ሸለቆ ስነ ምህዳር አካባቢ በበርካታ ስነ-ህይወታዊና ውሃ ሃብት የሚታወቅና አሉን የምንላቸው ኃይቆቻችንም የሚገኙበት ሲሆን ካለው ሃብት አንጻር በርካታ አካላትን የሚጋብዝና በአየር ንብረት ስርጭት ለውጥ፣ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ ሙቀት መጨመር፣ ለግብርና የሚታረሰው መሬት መጨመርና የከተሞች መስፋፋት ምክንያት ችግሮች እየገጠሙት መሆኑን በመረዳት የጥናት ማዕከሉ ተመራማሪዎች ከስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ጽ/ቤትና ከሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት ጋር በመሆን ዘላቂና ተፈጥሮን በተፈጥሮ ለማከም የሚረዳ የምርምር ውጤት ይፋ በማደረግ የመፍትሄው አካል በመሆን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሙሉጌታ ዳዲ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የጥናት ማዕከሉ ተመራማሪ ስልጠናውን መስጠት ሲጀምሩ እንደተናገሩት የምርምር ውጤቱ ዓላማ በተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና ደለል እንዲሁም የተለያዩ ችግሮች ያሉበትን መሬት ሳይንሳዊና ተፈጥሮአዊ በመሆነ በኢኮኃድሮሎጂመንገድ ለማከም ናለማልማት፣ ጎርፍን ለመቆጣጠር፣ ደለል ለመያዝ የሚረዳ ሲሆን የምርምር ግኝቱም በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ታትሞ በቅርቡ ለሳይንሱ ማህበረሰብ ተደራሽ እንደሚሆን ገልፀው ሰልጣኞችም አሁን እየሰራን ያለውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ማሻሻል ወይም መቀየር አስፈለገ፣ አዲሱን የኢኮኃድሮሎጂ ማሻሻያ ስርዓት ለመረዳት እና አዲሱ የአሰራር ስርዓትም ምን እንደያዘ፣ ለምን እና እንዴት መተግበር እንደሚችል ግንዛቤ ያገኛሉ ብለዋል፡፡
ስልጠናውም ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ እና በቀጣይም የአስራር ስርዓቱ ማንዋል ተዘጋጅቶ ስራ ላይ እንደሚውል ለማወቅ ተችሏል፡፡