የስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል በዝዋይ ተፋሰስ ውስጥ የተደረጉ የምርምር ውጤቶችን ይፋ አደረገ

የስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል በዝዋይ ተፋሰስ ውስጥ የተደረጉ የምርምር ውጤቶችን ይፋ አደረገ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ሽግግር ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕ/ጽ/ቤት የስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል በማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ ዝዋይ ተፋሰስ የመሬት አጠቃቀም፣ የመሬት ሽፋን ለውጥ፣ የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት ፣ የግብርና ኬሚካል ብክለት እና ተጓዳኝ አደጋዎች የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ  በተመለከተ የተደረጉ ምርምር ውጤቶች ለባለድርሻ የማሳወቂያ እና ግንዛቤ የማስጨበጫ መድረክ በመቂ ከተማ በታህሳስ19/2014ዓ.ም ተካሄደ፡፡

አቶ በጎነት ዳሌ የጥናት ቡድኑ አባል እንደገለጹት ጥናቱ በአምስት የተፋሰሱ አካላት ማለትም በቡኢ፣ ቡታጅራ፣ ቆሼ፣ መቂ እና ዝዋይ ባለፉት 30 ዓመታት የመሬት አጠቃቀምና የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት ምን እንደሚመስል የፈተሸ ሲሆን ከዓመት ዓመት ዝናብ እየቀነሰ መምጣቱን፣ የመሬት አጠቃቀምና በገፀ-መሬት ላይ የሚፈሰው የውሃ መጠን መጨመሩን እና የውሃ ሀብት መቀነሱን የጥናት ውጤቱ በማሳየቱ ይሄንን ለመቅረፍ የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር ስርዓትና የማህበረሰብ መረጃ ማዕከል መደራጀት እንዳለበት፣ አካታች ዕቅድ መታቀድ እና ሳይንሳዊ ጥናት ሊተገበር እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

አቶ ዳንኤል ወ/ሚካኤል የጥናት ቡድኑ አባል  በዝዋይ ሀይቅ ዙሪያ በሚካሄዱ የሀይቅ ዳርቻ መስኖ እርሻን በተመለከተ የተደረገውን ምርምር ውጤት እንደተናገሩት የአበባ፣ ሽንኩርት እና ቲማቲም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሲባል የኬሚካል አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ኬሚካሉ በምግብ ሰንሰለቱ ላይ ችግር በማስከተል የሰው ልጆችን እየጎዳ እንደሆነ፣ የመሬቱ ምርታማነት እየቀነሰ መምጣቱን እና አፈራርቆ የተለያዩ ምርቶችን ያለማምረት ችግር እንዳለ ገልጸው በአፋጣኝም ለዚህ ችግር መፍትሄ እንደሚያስፈልግ እንዲሁም በግል ኩባንያዎች ላይም የኬሚካል አጠቃቀማቸው ላይ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በፕሮጀክቱ የማህበረ- ኢኮኖሚያዊ ቡድን አስተባባሪ  የሆኑት ዶ/ር አለም አንተ አመራ በተፋሰሱ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት መጎዳት በአካባቢው ያመጣውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ገልጸው  ባለድርሻ አካላትም ይሄንን ተረድተውና  ተገንዝበው ዘላቂ ልማት ለማምጣት በጋራ መሰራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በፕሮግራሙም በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሚያዎችና ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቀረቡት የጥናት ውጤቶች እና ቀጣይ አቅታጫዎች ላይ ምክክርና ውይይት ተካሂዶ ፕሮግራሙ መጠናቀቁ ታውቋል፡፡

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et