የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሀገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሄደ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ መግባባት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር “የኢትዮጵያ ሰላም ፖሊሲ” እና “የውጪ ጣልቃ ገብነትና ብሔራዊ መግባባት ላይ የምሁራን ሚና” በሚል ርዕስ ታህሳስ 15/2014 ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
ክቡር ታዬ ደንደአ በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በመክፈቻ ንግግራቸው በአሁኑ ሰዓት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን መሪነት በኢትዮጵያ ልጆች ጀግንነት ወራሪውን ጁንታ በማስወገድ ለድል በቅተን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት በመብቃታችን እጅግ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አክለው እንደገለጹትም ኢትዮጵያ ሀገራችን ዕውቀት፣ ጀግንነት ሀብት ሁሉም ነገሮች አሏት፤ ሀገር በቀል ዕውቀት አለን አንድነታችንን የምናጠነክርበት፣ ነባር መድኃኒቶች አሉን የምንፈወስበት፣ የእጅ ጥበብና ባህላዊ ትውፊቶች አሉን የምንደምቅበት ነገር ግን አንድ ላይ ሆነን በመቀናጀትና በመደመር ወደለውጥ ጎዳና መሄድ ነው ያቃተን፡፡ በሀገራችን አዎንታዊ ሰላም እንዲሰፍን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከኃይማኖት ተቋማት ጋር እየሰራን ሲሆን ሀገር የሚገነባው በዕውቀት እንደመሆኑ ምሁራን አስፈላጊ ናቸውና በዛሬው ዕለትም የሚቀርበውን ረቂቅ የሰላም ፖሊሲ ምን እንደሚመስል ምሁራኑ ተረድተው የራሳቸው እንዲያረጉት፣ ሰነዱ የተሟላ እንዲሆን በመገምገም ግብዓት እንዲሰጡበት እና በሌላው በሚቀርበው ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ ተመርኩዘውም ኃሳብና አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ወቅት እንደገለፁት የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ሀገራዊ ጥሪን በመቀበል በመጀመሪያው ዙር ከ18 ሚሊየን ብር በላይ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከ45 ሚሊየን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ከደሞዛቸው ድጋፍ ማደረጋቸውን አውስተው ከዚህ በተጨማሪም በወሎ፣ በደብረብርሃንና በአፋር ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የአይነት ድጋፍ በአካል በመገኘት መደረጉን እንዲሁም የደም ልገሳና በሆስፒታላችን እና በደቡብ ዕዝ ለሚገኙ ተጎጂ ታካሚዎች ከህክምና በተጨማሪ ድጋፎች እተደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በዕለቱም የውጪ ጣልቃ ገብነትና ብሔራዊ መግባባት ላይ የምሁራን ሚና በሚል ርዕስ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር መልሰው ደጀኔ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲና ልማት፣ የጋዜጠኛነትና ኮሚውኒኬሽን መምህርና ተመራማሪ ፅሁፋቸውን ሲያቀርቡ የውጪ ሀገራት ጫናና ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ላይ ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የሚዲያ ጫና እና ሀገራዊ ምላሾች እንዲሁም የምሁራን ሚና፣ ተግባርና ኃላፊነት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰላም ፖሊሲን ሰነድ ደግሞ አቶ ሻንቆ ደሳለኝ በሰላም ሚኒስቴር የተጠሪ ተቋማት እና የስትራቴጂ አጋርነት ዳይሬክተር ጀነራል አቅርበው በተሳታፊዎችም ውይይትና አመርቂ አስተያየቶች ተሰጥቶባቸው ውይይቱ መጠናቀቁ ታውቋል፡፡
በምክክር መድረኩ ከ12 ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ ሰራተኞችና የተማሪ ተወካዮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡