የተቀናጀ የግብርና ገበያን እና የአየር ንብረት መረጃን ለማሰራጨት በዋለው መተግበሪያ ላይ ያተኮረ አውደጥናት ተካሄደ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከፋርም አፍሪካ ኢትዮጵያ ጋር በትብብር ሲሰራ የቆየውን እና በሀላባ፣ ሀዳሮና ዳሞት ጋሌ ወረዳዎች ላይ ለሚገኙ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ላይ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየውን የተቀናጀ የግብርና ገበያን እና የአየር ንብረት መረጃን ለማሰራጨት በዋለው መተግበሪያ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር አውደጥናት አካሂዷል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍስሃ ጌታቸው በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ግብርና የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ቢታወቅም በእውቀት የዳበረና በቴክኖሎጂ የታገዘ መረጃ መር የሆነ የግብርና ስራዎችን ስለማንከተል ሀገሪቱም ሆነች አርሶ አደሮቻችን ሳይሆኑ የሚጠቀሙት በምርት ሰንሰለቱ እሴት ሳይጨምሩ በአምራቹ እና በተጠቃሚው መሃል ላይ ያሉት ደላሎች እና ነጋዴዎች በመሆናቸው ለአርሶ አደሮቻችን የግብርና ገበያን እና የአየር ንብረት መረጃን ተደራሽ ማድረግ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃን በማግኘት የመደራደር አቅማቸውን ከማሳደጉም በላይ የተሻለ ውሳኔ ላይ ለመድረስና አማራጭ የገበያ ቦታዎችን እንዲመርጡ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ ባለሙያ ወ/ት ሜቲ ተስፋዬ የዚህን መሰሉን መተግበሪያ በሰፊው ለማዳረስ ደካማ መሰረተ-ልማት መኖሩ፣ በቂ እውቀትና ገንዘብ አለመኖሩና የመረጃ ማስተላለፊያው ደካማ መሆን ማነቆ እንደሆነ ገልፀው አሁን ተግባራዊ ባደረግነው መተግበሪያ መነሻ በማድረግ በቀጣይ የአርሶ አደሮቹን፣ የገብያ ቦታንና የምርቶቹን ቁጥር የመጨመር፣ የግብርና ገበያን እና የአየር ንብረት መረጃ ስርጭትን የማሻሻል እና መተግበሪያው ገቢ እንዲያመነጭ የማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በአውደ ጥናቱም በመተግበሪያው ከ5400 በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን የተተገበረው የመተግበሪያ ቀጣይነት፣ ተደራሽነት፣ ዘላቂነትና በባለቤትነት የማስቀጠል ስራዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎባቸውና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተቀምጠው አውደጥናቱ ተጠናቋል፡፡