የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የኢትዮጵያዊ ሀገር ፍቅር እና የምዕራባውያን ዜና አውታሮች ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በሚል ርዕስ የምክክር ዓውደ ጥናት አካሄደ፡፡
በዓውደ ጥናቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር መሳይ ሀይሉ የተማሪዎች አገልግሎት እና የአስተዳደር ሰራተኞች ም/ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆችዋ አንድነትና ፍቅር ነፃነትዋን በማስጠበቅ የጥቁርን የጨለማ ዘመን በብርሃን በመተካት የጀግንነት ታሪክን ከራስዋ አልፋ ለሌሎች አፍሪካውን ያጎናፀፈችና ታላቅ ታሪክ ያላት ሀገር መሆንዋን አውስተው አሁንም በላቀ ሀገራዊ አንድነት እና ፍቅር ይህንኑ ታሪክ ለማስቀጠል የራሳችንን የውስጥ ችግር በራሳችን መፍትሄ እየሰጠን ለማስቀጠል ህዝባችን እየተጋ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ አክለውም ዩኒቨርሲቲያችንም ከተሰጠው ተልዕኮ በተጨማሪ የገጠሙንን ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን በመገንዘብ የሀገራችንን ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር ለማስቀጠል የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ ከማድረግም በተጨማሪ ምሁራኖቻችን ያላቸውን ዕውቀት በመጠቀም በርካታ ሳይንሳዊ ምርምሮችን በማድረግ የመፍትሄ ኃሳቦችን በማመንጨትና በህዝባችንም ላይ የማስረፅ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ዶ/ር ዳኜ ሽብሩ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ እንደገለፁት ከአድዋ ድል በኃላ ቅኝ ገዢዎችና የእነሱ ተባባሪዎች በተደጋጋሚ ሀገራችንን ለመውረርና ለማስገዛት ሞክረው አልተሳካላቸውም ፤ ይህም ሊሆን የቻለው ጀግንነት እና አልገዛም ባይነት እኛ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን ከአያቶቻችንና ከአባቶቻችን የወረስነው ትልቁ እሴታችን በመሆኑ ነው ያሉ ሲሆን የመድረኩ ዓላማም የአርበኝነት ስሜትን ለመቀስቀስ፣ የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ታሪክን ለማስታወስ፣ የምዕራባዊያን የዜና አውታሮች እንዴት በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ገብተው በሃሰተኛ ዜና እያወኩን እንደሆነ ለማሳየት እና ሀገራችን አሁን የገጠማትን ፈተና እንዴት መቋቋምና መወጣት እንደምትችል አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ለመወያየት ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩም በተጠቀሱት ርዕሶች ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበውና ውይይት ተደርጎባቸው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡