የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማራማሪ እና ወዳጆቻቸው ለመከላከያ ሰራዊት ከ290 ሺህ ብር በላይ የአይነት ድጋፍ አበረከቱ።
መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ የበኩላችንን እንወጣ በማለት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማራማሪ ፕሮፊሰር ካሳሁን አስማረ እና ወዳጆቻቸው በግል ጥረታቸውና በራሳቸው ተነሳሽነት ያሰባሰቡትን ከ290 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ በሀዋሳ ደቡብ ዕዝ አጠቃላይ ሆስፒታል ለሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት አባላት አበረከቱ፡፡
ፕሮፊሰር ካሳሁን እንደገለፁት ይህ ድጋፍ ለሀገር ግንባታ እየተዋደቀ እና ህይወቱን እየገበረ ላለው መከላከያ ሰራዊት ቢያንስ እንጂ አይበዛበትም ያሉ ሲሆን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን በሚችለው መጠን ድጋፍ ማድረግ ያለበት መሆኑን አውስተው የዚህ መሰሉ ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
ኮረኔል መሐመድ ከድር የደቡብ ዕዝ አጠቃላይ ሆስፒታል ኃላፊ እንደገለፁት በዚህ መልኩ የሚደረግልን ድጋፍ ህዝባችን ከእኛ ጎን እንዳለ ከማሳወቁም በላይ እኛም ለተሰለፍንበት ሀገር የማዳን ዓላማ ዕውቀታችንን፣ ክህሎታችንን፣ ብሎም ህይወታችንን ሳንሰስት እንድናበረክት ያበረታናል ያሉ ሲሆን ህዝባችንም ዘመቻው እስኪጠናቀቅ ድረስ በሀሳብ፣ በዕውቀት፣ በጉልበት፣ በአይነት እና በመሳሰለው ከጎናችን በመሆን መደገፍ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በዕለቱም ከ290 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ 7 ሰንጋዎች፣ 10 ፍየሎች፣ የታሸጉ ውሃዎች፣ጁሶች፣ 60 ሌትር ዘይት እና 2000 ሺህ እንቁላል ለመከላከያ ሰራዊቱ መበርከቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡