በትምህርት ሚኒስቴር መዳቢነት ለተመደቡ መምህራን እና ተማሪዎች አቀባበል ተደረገ

አለመረጋጋት ከተከሰቱባቸው ዩኒቨርስቲዎች በትምህርት ሚኒስቴር መዳቢነት በማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ትምህርት ዘርፍ ለተመደቡ መምህራን እና ተማሪዎች አቀባበል ተደረገ፡፡

ሀዋሳ፤ ታህሳስ02 ፤2014 (ጄ.ሲ.ሳ) በትምህርት ሚኒስቴር መዳቢነት ከመቐለ እና አክሱም ዩኒቨርሲቲ ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ስር ባሉ ትምህርት ክፍሎች ለተመደቡ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው አለመረጋጋት ላለፉት ጥቂት የማይባሉ ወራት የመማር ማስተማር ስራው መቋረጡ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ትምህርት ሚኒስቴር በበይነ መረብ ባደረገው ምዝገባ መምህራኑ እና ተማሪዎቹ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች እንዲመደቡ ተደርጓል፡፡

በዚህም መሰረት በማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ በእንግሊዘኛ ቋንቋ እና ስነ-ፅሁፍ፤ አንትሮፖሎጂ እንዲሁም በጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን የትምህርት መስኮች ለተመደቡ መምህራን እና ተማሪዎች በጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ማህበር (ጄ.ሲ.ሳ) አዘጋጅነት የእንኳን ደህና መጣችሁ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ መምህራኑም ሆኑ ተማሪዎቹ የደረሰባቸው የስነ-ልቦና ጫና እንደ ሀገር የተጋረጠብን ችግር አካል መሆኑን በመገንዘብ የባከነውን የመማር መስተማር ጊዜ ለማካካስ በሚወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች የበኩላቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ተጠቁሟል፡፡ በተለይም በዩኒቨርስቲው በሚኖራቸው ቆይታ የዩኒቨርስቲውን ህግ በማክበር እና ከዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ጋር ጠንካራ የተግባቦት ባህልን በማዳበር የባከኑ የትምህርት ጌዜያቶቻቸውን ሊያካክሱ እንደሚገባም የጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህራንን እና ተማሪዎችን በመወከል የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የት/ት ክፍሉ ሀላፊ መምህርት ህይወት ዮሀንስ አሳስበዋል፡፡

ከመማር እና ማስተማር ርቀው የቆዩባቸውን አስቸጋሪ ጊዜያቶች በአዲስ ሞራል እና ጉልበት እንዲያካክሱ ጥሩ መነቃቃትን የፈጠረ አቀባበል እንደተደረገላቸው የተመደቡት መምህራን እና ተማሪዎችም በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል፡፡ በፕሮግራሙም የጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ት/ት ክፍል መምህራን እና ተማሪዎች፤ የተማሪ መማክርት ተወካዮች፤ ከመቐለ እና አክሱም ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ መምህራን እና ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ዘገባው የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ት/ት ክፍል ተማሪዎች ማህበር(ጄ.ሲ.ሳ) ነው፡፡

ለሃሳብ እና አስታያየት://t.me/HUJCSA/0913380454 እዉነቱን በኃላፊነትና በሚዛናዊነት እንነግራችኋለን!!

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et