የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኩል የተሰሩ የስንዴ ምርጥ ዘር ማሳዎችን ጎበኙ

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኩል የተሰሩ የስንዴ ምርጥ ዘር ማሳዎችን ጎበኙ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ም/ቴ/ሽ/ም/ጽ/ቤ/ት በማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አማካኝነት በሲዳማ ክልል ጫሮኒ ወረዳ  የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት ማሳዎችን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ በተገኙበት በታህሳስ2/2014ዓ.ም ለባለድርሻ  አካላት አስጎበኘ፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ እንደተናገሩት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአከባቢውን ማህበረሰብ በዘመነ መንገድ በምርምር ውጤቶችና በዕውቀት ለማስታጠቅ ዋነኛ ዓላማ አድርጎ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ህብረተሰቡም በበኩሉ በተለይም የወጣቱን ክፍል ዩኒቨርሲቲያችንም ሆነ የክልሉ መንግስት በሚደግፍበት አቅጣጫ ተባባሪ በመሆን ራሱንና አከባቢውን እንዲለውጥ ማበረታታትና መምከር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ አሁን በተጎበኘው የስንዴ ምርጥ ዘር ማሳ አያያዝ ላይ የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ የጠቆሙት ፕሬዝዳንት ካሁኑ ትምህርት በመውሰድ በሚቀጥለው ጊዜ የተሻለ ውጤት ለማምጣት መትጋት፣ ከትንሽ መሬት ብዙ ምርት በመሰብሰብ ተጠቃሚ ለመሆን መጣር እና ይህን ምርጥ ዘር ለሌሎች አካባቢዎችም ለማድረስ ዓላማ ይዞ መሥራት አርሶ አደሩን እራሱን ስለሚመለከት ዛሬ ትልቅ ግንዛቤ መፈጠር አለበት በማለት ከጠጥቻ፣ ከሁላና ከጭሮኔ ወረዳዎች ለተሰበሰበ ህዝብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ አክለውም የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ባህላዊውን መንገድ ብቻ ተከትሎ ኑሮን ማሻሻልም ሆነ መለወጥ ስለማይቻል የዘመኑን ዕውቀትና ቴክኖሎጂ መከተል አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን በቅጡ መረዳት ተገቢ መሆኑን ህብረተሰባችን ማወቅና የተመራማሪዎችንና የሙያተኞችን ምክር በአግባቡ ተቀብሎ በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ከዚህ መነሻነትም አመለካከታችን፣ አሠራራችንና አመራራችንም ፈጽሞ ከዘመኑ ጋር የተቆራኘ መሆን ይኖርበታል ያሉ ሲሆን እኛም እንደተቋማችን ባለሙያዎችን በማሰልጠንና በየጊዜው የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮች በሚገኙበት ሁኔታ ላይ የበኩላችንን እናደርጋለን ሲሉ መልዕክታቸውን አጠቃልለዋል፡፡  

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን ማህበረሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማሻሻል፣ ችግሩን ለመፍታት  እና የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ በርካታ ስራዎችን በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና እና በመሳሰሉት የፈጠራ ስራዎችን እያበረከተ እንደሆነ እና ባዩትም እጅግ መደሰታቸውን ገልጸው በክልሉ የሚታዩት  አንዳንድ ችግሮች ተራ ሳይሆኑ የምሁራንን ዕይታ፣ ምርምርና ተግባራዊ ተሳትፎ የሚጠይቁ እንደመሆናቸው በቀጣይም ከክልሉ መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ክፍተኛ ዕምቅ አቅም መኖሩን አውስተዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ክልሉም  ዩኒቨርሲቲው በዚህ ወረዳ ያበረከተውን የስንዴ የምርጥ ዘር ብዜትም ሆነ በሌሎች ወረዳዎች እየሰራ ያላቸውን የምርጥ ዘር ብዜቶች ለህብረሰተቡ በብዛት ውጤቱ ይደርስ ዘንድ እና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀው በማህበረሰቡ ዘንድም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የመቀበል እና ወደ ስራ ለመግባት የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን አውስተው ዩኒቨርሲቲው እስካሁን በክልሉ ላመጣቸው አስተዋፅኦዎች እና እየሰራቸው ላላቸው ተግባሮች በክልሉ ህዝብ እና መንግስት ስም አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡

የም/ቴ/ሽ/ም/ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በበኩላቸው እስካሁን በተለያዩ ወረዳዎች የተሰሩ እና እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች ያብራሩ ሲሆን በጭሮኔ ወረዳም ሾሪማ የተሰኘ 40 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ለ80 ሞዴል አርሶ አደሮች ተሰራጭቶ በኩታ ገጠም እንዲያርሱ መደረጉን እና ይህ ምርጥ ዘርም ተሰብስቦ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ለሌሎች አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር ሆኖ እንዲሰራጭ እውቅን እንዲያገኝ ከሲዳማ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር እየተሰራ ያለ ሲሆን ይህ ስራ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና በሚቀጥሉት ዓመታት የዘር እጥረት ችግርን በመጠኑም ቢሆን የሚቀንስ ይሆናል ብለዋል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et