የትምህርት ኮሌጅ “ፍትሃዊ፣ አካታች እና ጥራት ያለው ትምህርት ለዘላቂ ልማት“ በሚል ርዕስ ሃገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ አካሄደ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ኮሌጅ “ፍትሃዊ፣ አካታች እና ጥራት ያለው ትምህርት ለዘላቂ ልማት“ በሚል ርዕስ በትምህርት ላይ የተሰሩ የምርምር ውጤቶችን ለባለድርሻ አካላት ለማድረስ እና በቀረቡትም የምርምር ውጤቶች ላይ ለመምከር ሃገር አቀፍ የምርምር ጉባዔ ከህዳር24-25/2014ዓም ድረስ አካሄደ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር ፍስሃ ጌታቸው በመክፈቻ ንግግራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ከሚገባቸው 10 ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ አንዱ በመሆኑ በምርምር ዘርፉ ይህንን ራዕይ ለማሳካት በየኮሌጆችና በኢንስቲዩቶች የሚገኙ የምርምር ጆርናሎችን ብዛትና ጥራትን የማሻሻል፣ እነዚህን የምርምር ጆርናሎችና የምርምር ፕሮጀክቶችን የመከታተያ ስርዓትን ኦቶሜት የማድረግ እና የዩኒቨርሲቲውን ምርምር ከዩኒቨርሲቲዉ የድህረ ምረቃ ምርምሮች ጋር የማቆራኘት ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ፍስሃ አክለውም በሀገራችን በሙያቸው የላቁ በስብእናቸውም የጎለበቱ ምርጥ መምህራን ለሀገራችን ልጆች እንደሚያስፈልጉ እና የሀገራችንም ሁለንተናዊ እድገት ምሰሶ የሚሆኑት እነዚሁ መምህራን መሆናቸውን ገልፀው በመምህራን ትምህርትና በትምህርት አመራር የተለየ ትኩረት በመስጠት በሀገራችን የልህቀት ማዕከልና ተመራጭ ለመሆን ባለፈዉ አመት ሰርተን ባፀደቅነው የ 10 አመት ስትራቴጂክ እቅዳችን ላይ በግልጽ ያስቀመጥን ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃም የነገን ትውልድ ለመቅረጽ የሚያስችልና የአጠቃላይ ትምህርት ስርዓት ለዉጥ አካል የሆነውን የተማሪ መማሪያና የመምህሩ መምሪያ መጽሓፍትን ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ዶ/ር አብርሃም ቱሉ የትምህርት ኮሌጅ ዲን እንደገለፁት ኮሌጁ የትምህርት ፕሮግራሞቹን በማስፋፋት በአሁኑ ሰዓት በ57 የትምህርት ፕሮግራሞች 2436 ተማሪዎችን እያስተማረ ሲሆን ኮሌጁ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል የምርምርና ስርፀት ስራ አንዱ በመሆኑ በደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ፍትሃዊና አካታች የትምህርት ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችሉ በርካታ ምርምሮችን በግልና በቡድን በማካሄድ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ በዚህ ጉባዔም 4 የቡድን እና 4 የግል ምርምር ግኝቶች ቀርበው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግባቸው ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ጂሉ ኡመር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ እንዲሁም ፕ/ር ተስፋዬ ሰመላ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ጥናትና ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ቁልፍ መልዕክታቸውን ለተሳታፊዎች ያስተላለፉ ሲሆን ፕ/ር ተስፋዬም እንደተናገሩት የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ጥናት እንደሚያመለክተው እና ህዝብም እንደሚያውቀው በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በወላጆች፣ በትምህርት ቤት ባለቤቶች፣ አስተዳዳሪዎችና ኃላፊዎች ትብብር የሀገር አቀፍ ፈተናዎች እንደሚሰረቁ እና ኩረጃዎች መበራከታቸው፣ ትምህርት ተደራሽነት ላይ እንጂ ጥራት ላይ ትኩረት አለመሰጠቱ፣ የትምህርት ስርዓቱ ከሌላው አለም ሲወሰድ በልክ ተሰፍቶ በሚመጥን መልኩ ባለመከለሱ በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ጎኑ እንዲያመዝን ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በጉባዔውም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ፣ ከሲዳማ ክልሎች ና ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ መምህራኖች እና ባለሙያዎች መሳተፋቸውን እና በሁለቱ ቀናትም በቀረቡት ጥናቶች ላይ እንደሚወያዩና ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጡ ይጠበቃል፡፡