የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በዳሌ ወረዳ ደቡብ ቀጌ ቀበሌ የአርሶ አደሮች የመስክ በዓል አከበረ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ስር የሚገኘው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አዳዲስ መስራች የጤፍ ዝርያዎችን ለማስፋት በሞዴል አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ማሳ ላይ የተሰሩ ስራዎችን ለመገምገም በሲዳማ ክልል ዳሌ ወረዳ ደቡብ ቀጌ ቀበሌ የአርሶ አደሮች የመስክ በዓል በህዳር11/2014 ዓ.ም አከበረ፡፡
ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት በመክፈቻ ንግግራቸውእንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ መንደር ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችን የተለያዩ ቴክኖሎጂን ተጠቃሚ ለማድርግ እና ኑሯቸውን ለማሻሻል የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን ለአርሶ አደሩ የማስተዋወቅ እና የማላመድ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ዶ/ር ታፈሰ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በያዝነው ዓመትም እንደተለመደው ለቅድመ ማስፋት ስራ የሚሆን 20 ኩንታል ጤፍ በሎካ አባያ፣ ዳሌ፣ ደራራ እና ወንዶ ገነት ለሚገኙ 38 ሞዴል አርሶ አደሮች፣ 40 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር በሁላ፣ ጭሮኔ፣ ጤጥቻ እና አርቤጎና ለሚገኙ 60 ሞዴል አርሶ አደሮች በተጨማሪም በፕሮቲን የበለጸገ ፖይነር የተሰኘ 40 ኩንታል በቆሎ ምርጥ ዘር በወንዶገነት፣ ዳሌና ሎካ አባያ ለሚገኙ 120 አርሶ አደሮች በነጻ መሰራጨቱን ጠቅሰዋል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም ሚሰራጩ ምርጥ ዘር ዝርያዎች በተባይ እና አረም እንዳይጎዱ ለማድረግ ከ130 ሊትር በላይ ጸረ- ተባይ ኬሚካል እና 18 የጸረ- ተባይ ኬሚካል መርጫ መሳሪያዎች በአራት ወረዳዎች መሰራጨቱን እና የእንስሳት መኖ ችግርን ለመፍታት የሚሰራውን ስራ ለማገዝ የተለያዩ የመኖ ዝርያዎችን በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ እያለማ በመሆኑ በሚቀጥሉት ዓመታት ለአርሶ አደሮች የማስተዋወቅና የማላመድ ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የአርሶ አደሮቹ ማሳዎች ከተጎበኙ በኃላ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ እና የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በጤፍ ማስፋት ሂደት ላይ የታዩ ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮችን በመገምገምና ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡