በወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ለኮሌጁ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ መመህራኖችና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ በስነ ምግባር ግንባታ፣ በተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ሰነድ ላይ እና በመልካም አስተዳደር ግንባታ ዙሪያ ለከፍተኛ ኃላፊዎች፣ መመህራኖችና ባለሙያዎች ከህዳር 2-3/2014 ዓም ድረስ የስልጠና እና ምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
ዶ/ር ሞቱማ ቶሌራ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት ኮሌጁ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ላይ ላለፉት 43 ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ጉልህ ድርሻን እየተወጣ እንዳለ ጠቅሰው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብለው ከተለዩ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደመሆኑ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ድግሪ ፕሮግራሞች እና ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ያሉትን ሀብቶቻችንን ከብክነት ነጻ በሆነ፣ ለታቀደለት አላማ እንዲውል ከማድረግ አኳያ፣ ስነምግባር በተላበሰ መልኩ ተገልጋይን ለማስተናገድ እንዲሁም በየወቅቱ የሚወጡ ህጎች እና ደንቦችን ተፈጻሚ ለማድረግ የዚህ መሰሉ የስልጠና እና የምክክር መድረክ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የኮሌጁ ዲን እንደገለጹትም ይህ ስልጠና እና የምክክር መድረክ ሁሉንም ባካተተ መልኩ ከፍተኛ ኃላፊዎችን፣ መመህራኖችንና ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ በመሆኑ ተሳታፊዎችም የሚነሱት ኃሳቦች በስራዎቻችን እና በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ምን ለውጥ ያመጣሉ የሚለውን ግብዓት በመውሰድ ወደፊት ተግባራዊ እንዲያደርጉት ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ፕሮግራም በመሆኑ ተሳታፊዎች ለፕሮግራሙ ትኩረት በመስጠት በአግባቡ እንዲሳተፉ ለማሳሳብ እወዳለሁኝ ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ መጀመሪያ ዕለት በስነ-ምግባራዊ የአመራር ክህሎት ዙሪያ በአቶ ዳግማዊ አላምረው በፊደራል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ባለሙያ ሰነዶች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን በሁለተኛውም ቀን በአቶ ከበደ ኩማ የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመልካም ምግባርና የሞራል ግንባታ፣ በአዲሱ የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና አዋጅ፣ በዕቅድና ሪፖርት አዘገጃጀት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቶ እንዲሁም በተነሱ ኃሳቦች ላይ ውይይት ተካሂዶባቸው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡