የአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በ2014 ዓ.ም ሩብ ዓመት አመረቂ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገለፀ
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት የተሰጡትን ተልዕኮዎች ከግብ ለማድረስ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጾአል፡፡ በዚህ መሠረት በ2014 በጀት ዓመትም የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን በመገምገም አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ወገኔ ማርቆስ ኮሌጁ እንደሀገር በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የ2013 ዓ.ም ተመራቂዎችን በያዝነው ዓመት መስከረም ወር ካስመረቅን በኃላ ተማሪዎቻችን ተቀብለን
እያስተማርን ነው ብለዋል፡፡
ኮሌጁ የማህበረሰቡን ችግር ይፈታሉ በተባሉ ሰባት ምርምሮች ላይ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ሲሆን በሲዳማ ክልል ከሚገኙ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ውል በመግባትም በርካታ ስልጠናዎች እየሰጠ እና የእውቀት ሽግግር እያደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ ለኮሌጁ መምህራንንም እራሳቸውን እንዲያበቁ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ኮሌጁ ጥናቶችን በማድረግ የጊዜን፣ ጉልበትን እና የሀብት ብክነትን ማስቀረት የሚችል በአይነቱ አዲስ የሆነውን የንብረት አስተዳደር መተግበሪያ በኮሌጁ ባለሙያ በማሰራት መምህራኖች እና ባለሙያዎች ተግባር ላይ እንዲያውሉት ስልጠና እየተሰጠ
መሆኑንም የኮሌጁ ዲን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ወገኔ ማርቆስ አክለውም የሀብት ብክነትን በማሰቀረት ለማስተዳደር አመቺ እና ሁሉንም አገልግሎት ለተማሪዎች ለመስጠት የአንድ ካርድ ስርዓት ለመተግበር የሚያስችለውን ባርኮድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀው ተማሪዎችም የሚዝናኑበትና ጤናቸውን የሚጠብቁበት የተለያዩ ሜዳዎች እና ካፍቴሪያዎች
መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ኮሌጁ ያሉትን ተሽከርካሪዎች ሲበላሹ የሚሰሩበትና የሚጠገኑበት፣ ንፅህናቸው የሚጠበቅበትና የሚቆሙበት ዘመናዊ ጋራዥ በማስገንባቱ ከዚህ በፊት ይወጣ የነበረውን የገንዘብ ወጪ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በዚህ ሙያ ለሚሰማሩ ባለሙያዎችም የስራ ዕድል በመፍጠር የእውቀትና የሙያ ክህሎት ሽግግር ለማድረግ እንደሚረዳ ዶ/ር ወገኔ ገልፀው ወደፊት ኮሌጁ እራሱን ችሎ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ከወዲሁ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡