በእንሰት ተክል ምርታማነትና አጠቃቀም ዙሪያ የምክክር አውደ-ጥናት ተካሄደ

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሲዳማ ጥናት ተቋም ከምርምርና ቴ/ሽ/ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በእንሰት ተክል ምርታማነትና አጠቃቀም ዙሪያ ላይ የምክክር አውደ-ጥናት  በጥቅምት 11/2014ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካሄደ፡፡

ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በመክፈቻ ንግግራቸው  ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከመደበኛው በጀት በተጨማሪ በትብብር ፕሮጀክቶች እና ሀገር በቀል እውቀቶችን በማቀናጀት እና በመጠቀም በርካታ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን እንሰት ተክልም በደቡብ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ከባህላዊ ምግብነት፣ ለቤት መስሪ፣ ለምንጣፍና ለከብቶች መኖ ከመሆን አልፎ ዘመናዊና ተወዳጅ የምግብ ዓይነት እየሆነ ቢመጣም ምርታማነቱን እና አጠቃቀሙን ከሀገር በቀል እውቀቶች ጋር በማያያዝ ከማዘመን አኳያ ውስንነቶች ስላሉ የዚህ መሰሉ የምክክር መድረክ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲሁም በዘርፉ ለሚደረገው ቀጣይ የምርምር ስራዎች ይረዳናል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቁልፍ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደተናገሩት በእንሰት ተክል ምርታማነትና አጠቃቀም ማሻሻልን የተመለከቱ የማስፋፊያ አገልግሎቶች አለመተግበራቸው፣ ተክሉ የሚያስገኛቸው አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ጠቀሜታቸው በዝርዝር አለመታወቃቸው፣ መረጃዎች ተቀምረው አለመያዛቸው፣ ምርቱን በሀገር አቀፍ ብሎም ወደ አለም አቀፍ ገበያ በሰፋት ያለማስተዋወቅ ሰብሉ ላጋጠመው መገለል አይነተኛ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ፈለቀ አክለውም ይሁንና ጉድለቶችን በአግባቡ ሞልቶ ጠቃሚ ተግባር ማከናወን እንዲቻል የዚህ መድረክ መዘጋጀት አንዱ ማሳያ ሲሆን የማስፋፊያ ማዕቀፍ መተግበር፣ የእንሰት ጀነቲክ ሀብት ጥበቃ ዘዴን መተግበር፣ እንሰትን ጉዳይ በስርዓተ-ትምህርት ማካተት፣ የምር ጥራትን ለማሳደግ እሴት መጨመር፣ ጠንካራ የገበያ ትስስር መፍጠር፣ በትብብር መስራት፣ የልህቀት ማዕከል መመስረት እና ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ቴክኖሎጂ ነክ ፕሮጀክቶችን በጥድፊያ ከመተግበር መቆጠብ በዘርፉ ወደምናልመው ግብ ለመድረስ እንደሚረዱን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙም ላይ ዩኒቨርሲቲው በእንሰት ምርምርና ልማት ላይ ያበረከታቸው ጉዞዎች እና የተለያዩ የምርምር ስራዎች በዘርፉ ተመራማሪዎች ቀርበው ችና ውይይት ተካሂዶባቸው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

 

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et