የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ2013ዓ.ም ሲያስተምራቸው የነበሩትን የመጀመሪያ፣የሁለተኛ እና የሶስተኛ ድግሪ 6800 በላይ ተማሪዎችን በመስከረም 08/2014ዓ.ም አስመርቋል፡፡
ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በዕለቱ ተገኝተው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብለው ከተለዩት 8 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 10 ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የመሆን ራዕይ አንግቦ በመስራት ላይ እንዳለ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው በ8 ኮሌጆች እና በ3 ኢንስትቲውቶች 103 የመጀመሪያ ድግሪ፣ 136 የሁለተኛ ድግሪ፣ 53 የሶስተኛ ድግሪ እና 11 የስፔሻሊቲ ፕሮግራሞችን በመክፈት ከ40000 በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት በሰባት ካምፓሶች እያስተማረ የቆየ ሲሆን እንደሚታወቀው ያልተጠበቀው የኮሮና ወረርሽኝ በመከሰቱ የትምህርት አሰጣጡና የምረቃ ፕሮግራሞቹ ከተለመደው ጊዜ ቢዘገይም ይህንንአስቸጋሪ ጊዜና ወቅት በመቋቋምና በማለፍ ለዛሬዋ ቀን በመድረሳቸው ተመራቂ ተማሪዎችን እና የተመራቂ ቤተሰቦችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዋና አፈ ጉባኤ በዕለቱ ተገኝተው ዛሬ እጅግ ከፍተኛ ትዕግስት፣ ጥረት እና ልፋት የሚጠይቀውን ረዥሙን የትምህርት ጎዳና በቤተሰቦቻችሁና በዩኒቨርሲቲያችሁ፣ ከሁሉም በላይ በራሳችሁ እልህ አስጨራሽ ጥረትና ትጋት በድል አልፋችሁ የራሳችሁን፣ የማህበረሰባችሁንና በአጠቃላይ የሀገራችሁን ብሩህ ዕድል ለመወሰን ትበቁ ዘንድ ከምታልፉባቸው እርከኖች መካከል ወሳኝ የሆነውን ምዕራፍ በስኬት አጠናቃችሁ ለቀጣዮቹ አንጋፋ ምዕራፎች በምትዘጋጁባት በዛሬዋ ዕለት ከመሃከላችሁ ተገኝቼ የደስታችሁ ተካፋይ በመሆኔ ታላቅ ደስታ ይሰማኛልና እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
አፈ ጉባኤው አክለውም እናንተ የዛሬው ዕለት ተመራቂዎችም ራዕይ በመሰነቅ፣ ትክክለኛና ጤናማ ስነ-ምግባር፣ ጠንካራ የስራ ባህልና ተነሳሽነትን በመገንባት በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ የቀሰማችሁትን ትምህርት ከተግባር ጋር በማገናዘብ በምትሄዱበት ቦታና በምትሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ ብልሹ አሰራሮችን በመጸየፍ፣አብሮነትን፣ አንድነትን ፍቅርንና ሰላምን በመስበክ ጠንካራ የስራ ባህል በማጎልበት የጋራ ቤታችሁን የሆነችውን ሀገራችሁ ኢትዮጵያን እንድትገነቡ አደራ እያልኩ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁኝ ብለዋል፡፡
በምረቃ በዓሉም ላይ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት በወሰነው መሰረት ለአርቲስት አዱኛ ዱሞ የክብር ዶክትሬት ድግሪ ተሰጥቷቸዋል፡፡