የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክት ከፌደራል ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን፣ ከጂአይዜድ እና ባለድርሻ አካላት ጋር ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም በሀዋሳ ሀይሌ ሪዞርት የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ ይህም ተፈጥሮን መሰረት ባደረገ መልኩ የአረንጓዴ መሰረተ ልማትን በመዘርጋት የሀዋሳ ሀይቅን ለመታደግ የሚያስችል ምክክር ሲሆን በዕለቱ የመስክ ምልከታ ፕሮግራም አድርጓል፡፡
ዶ/ር አዳነች ያሬድ የፌደራል ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዳይሬክተር በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት የስምጥ ሸለቆ ይቆች ተፋሰስ ለሀገራችን በርካታ ጥቅም እየሰጡ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች የሚገኙበት ተፋሰስ ቢሆንም በተፋሰሱ ላይ በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ተግዳሮቶች እየደረሱ ይገኛሉ ስለሆነም ያለውን ጠንካራ ጎን አጠናክሮ ለመቀጠል ተግዳሮቶችን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታትና ለመቀነስ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር አዳነች አክለውም በዚህ መድረክ በሀዋሳ ንዑስ ተፋሰስ ውስጥ በተፈጥሮ ሀብታችን ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በጥልቀት ለመረዳት፣ ችግሮቹን በጋራ ለመወያየት እና ለመፍታት እንዲሁም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ቅንጅታዊ ስራ እንዲከናወን በማድረግ የበኩላችንን ሚና በመወጣት የሀዋሳ ሀይቅንም ለመታደግ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሙሉጌታ ዳዲ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የPLH-NaGI ፕሮጀክት አስተባባሪና ተመራማሪ እንደተናገሩት የፕሮጀክቱ ዓላማ የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና ደለል እንዲሁም የተለያዩ ችግሮች ያሉበትን መሬት ሳይንሳዊና ተፈጥሮአዊ በመሆነ በኢኮ ሃይድሮሎጂ መንገድ በማከም 600 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት፣ ከምግብ ዋስትና ጋር ማስተሳሰር፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር፣ ጎርፍን መቆጣጠር፣ ደለል ለመያዝ እና ለሌሎች ተመራማሪዎች ሰርቶ ማሳያ ለማድረግ መሆኑንን ገልጸዋል፡፡